ለህዝቦች ጥቅምና መብት መከበር እንደሚሰራ የአማራ ህልውና የኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
ለህዝቦች ጥቅምና መብት መከበር እንደሚሰራ የአማራ ህልውና የኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት አስታወቀ
ደብረብርሀን ጥቅምት 19/2011 በሀገሪቱ የተረጋጋና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የድርሻውን በመወጣት ለህዝቦች ጥቅምና መብት መከበር እንደሚሰራ የአማራ ህልውና የኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት አስታወቀ። ድርጅትቱ ከደብረ ብርሃን ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ጋር በደብረ ብርሃን ከተማ ውይይት አድርጓል። የድርጅቱ የህዝብ ግንኙነትና የማስታወቂያ መምሪያ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ መኮንን እንደገለጹት ድርጅቱ ሕብረተሰቡን በማስተባበር የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ ለማስቀጠልና ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን ጥቅምና መብት መከበር ይሰራል፡፡ " በአገሪቱ በአሁኑ ወቅት ለተፎካካሪ ፓርቲዎች የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመን ትግላችንን በሰላማዊ መንገድ በማስቀጠል ቀጣዩ ምርጫ ታማኝ፣ ነጻና ፍትሃዊ እንዲሆን ለማድረግ እንሰራለን " ብለዋል፡፡ " የፖለቲካ ፓርቲ መብዛት ለኢትዮጵያ አያወጣትም " ያሉት አቶ ተስፋዬ ከሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በመቀናጀት የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ወግ፣ የመቻቻል፣ የአብሮነትና የአንድነት ባህል ለማስቀጠል ተግተው እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡ በሀገሪቱ የተረጋጋና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ድርጅቱ የድርሻውን እንደሚወጣ የገለጹት አቶ ተስፋዬ፣ በመንግስት በኩልም እርስ በርስ ልዩነት የሚፈጥሩ ጉዳዮችን ማስወገድና ለማንነት ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ መስጠት እንደሚገባ ተናግረዋል። ማንኛውም አካል መብቱን ለማስከበር ሌላውን ቅር ማሰኘት የለበትም ያሉት ኃላፊው፣ ወጣቱም ትግሉን በህግና ደንብ መሰረት በሰላማዊ መንገድ ካላጠናከረ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝንም አስረድተዋል፡፡ ሌላው የድርጅቱ አመራር አቶ ተክሌ የሻው በተለያዩ አካባቢዎች በማንነት ጥያቄና በወሰን ይገባኛል ምክንያት የሚነሱ ሁከትና ብጥብጦችን ለማስቀረት ድርጅታቸው በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡ "በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየተስተዋለ ያለው መፈናቀል፣ ደም መፍሰስና ግድያም መቆም አለበት" ብለዋል፡፡ የየክልሉ ወጣቶች ለአገሪቱ እድገትና ለህዝቡ መብት መከበር ከመስራት ባለፈ ሀገሪቱን ከኋላቀርነትና ድህነት ለማላቀቅ መታገል እንዳለባቸው አስረድተዋል፤ " ድርጅቱም ለእዚህ የድርሻውን ይወጣል" ብለዋል፡፡ ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል ወጣት ረድኤት ወልደአማኑኤል በበኩሏ ለአገራዊ አንድነትና ልማት በመታገል የበለጸገች ሀገር ለትውልድ ለማስተላለፍ የድርሻዋን እንደምትወጣ ተናግራለች፡፡ " በክልሉ ያሉ በርካታ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ወጣቱን ከማወዛገብ ይልቅ ወደ አንድ በመምጣት የመከፋፈልና የማንነት ጥያቄ የተጋረጠባትን ኢትዮጵያ ወደ አንድ ማምጣት ይጠበቅባቸዋል" ብላለች፡፡ ወጣት ሲያምር ሰይፉ በበኩሉ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ በማቋቋምና በፖለቲካ እንቅስቃሴው የነቃ ተሳትፎ እንዲኖራቸው በማድረግ በኩል ድርጅቱ የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቋል፡፡ በምክክር መድረኩ ላይ የደብረ ብርሃን ከተማና አካባቢው ወጣቶች፣ ነዋሪዎች፣ ሽማግሌዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡