ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች ለውይይቱ ወደ ፍራንክፈርት እየገቡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች ለውይይቱ ወደ ፍራንክፈርት እየገቡ ነው
አዲስ አበባ ጥቅምት 19/2011 ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር ከነገ በስቲያ በሚካሄደው የውይይት መድረክ ለመሳተፍ በአውሮፓ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን የዳያስፖራ አባላት ወደ ጀርመን ፍራንክፈርት መግባት ጀምረዋል፡፡ ኢትዮጵያውያኑና በአውሮፓ ከሚገኙ 12 ኤምባሲዎች የተወከሉ ዲፕሎማቶች ፍራንክፈርት እየደረሱ ሲሆን መድረኩ “በአንድነት እንነሳ፣ ነገንም እንገንባ” በሚል መሪ ሃሳብ እንደሚካሄድ የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ የሚመራው ብሔራዊ ኮሚቴ ከበርሊን የኢትዮጵያ ኤምባሲና የፍራንክፈርት የቆንሲላ ጽህፈት ቤት እንዲሁም የዳያስፖራ አባላት ጋር በመሆን ለስነ ስርዓቱ ዝግጅቱን ማጠናቀቁ ተገልጿል። ኮሚቴው የእስካሁኑን ዝግጅትና አጠቃላይ ሂደት አስመልክቶ መግለጫ ይሰጣል ተብሎም ይጠበቃል። የፍራንክፈርቱ ዝግጅት የተሳካ እንዲሆንም 200 የበጎ ፍቃድ ሠራተኛ ኢትዮጵያውያን ተሳታፊ እንዲሆኑ ተደርጓል። ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አብይም ወደ ፍራንክፈርት ከተማ በማምራት ከመላው አውሮፓ ከተውጣጡ ከ25 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ጋር ኢትዮጵያን በጋራ እንዴት እንገንባ በሚልና መንግስት ዳያስፖራውን እንዴት ይደግፍ በሚል ውይይት ያካሂዳሉ ተብሎ ይጠበቃል። በአውሮፓ የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ የሚቋቋምበት ሁኔታ ሃሳብ መለዋወጥም ከአጀንዳዎች መካከል አንዱ እንደሆነም ተገልጿል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ከጥቂት ወራት በፊት በሰሜን አሜሪካ ያደረጉት ጉብኝት ቀጣይ ምዕራፍ የሆነው ይኸው መድረክ የአንድነትና የፍቅር ድልድይ በመገንባቱ የተፈጠረው የህብረት መንፈስ ለአገር ግንባታ ማዋል እንዲቻል ጥሪ ይቀርብበታል ተብሎ እንደሚጠበቅም ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።