ደብረ ብርሃን ከተማ በሰሜን ሸዋ ዞን በተካሄደው የአትሌቲክስ ሻምፒዮና በበላይነት አጠናቀቀ

32
ደብረብርሀን ጥቅምት 19/2011 በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በተካሄደው የአትሌቲክስ ሻምፒዮና በደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር አጠቃላይ አሸናፊነት ተጠናቀቀ። አስተዳደሩ ሻምፒዮናውን የበላይ ሆኖ ያጠናቀቀው በወጣት ሴቶች ስድስት ኪሎ ሜትር፣ በወጣት ወንዶች ስምንት ኪሎ ሜትር እንዲሁም በአዋቂ ወንዶች 12 ኪሎ ሜትር ተወዳዳሪዎቹ ቀዳሚነት በማግኘቱ ነው። በውድድሮቹ ጣርማ በር ወረዳ ሁለተኛ በመውጣት ሲያጠናቅቅ ፣ ዋዩ ወረዳ ደግሞ ሦስተኛ ሆኗል። ለአንድ ቀን በተካሄደው ሻምፒዮና ከዘጠኝ ወረዳዎች የተውጣጡ 63 ስፖርተኞች ተሳትፈዋል። የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ክላል ሳህለ ማሪያም በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ዞኑ ለአትሌቲክስ መስፋፋትና ማደግ አመቺ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና የአየር ንብረት እንዳለው ተናግረዋል። በአገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ ስፖርተኞችን እንዳፈራም አስታውሰዋል። የመርሃ ቤቴ ወረዳን ወክሎ የተሳተፈው ወጣት ዳዊት ሀብቴ በበኩሉ መንግሥት ስፖርቱን ለማበረታታት ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ ሊያደርግ ይገባዋል ብሏል። የደብረ ብርሃን ከተማን የተወከለችው ወጣት ዘበናይ ቸኮል በተሳተፈችበት ውድድር አንደኛ መውጠቷን ገልጻ፣በክልል ደረጃ በሚካሄደው ውድድር የተሻለ ውጤት ይዛ ለመመለስ ዝግጅቷ እንደምትቀጥል ተናግራለች። ስፖርት የሰላም መድረክ በመሆኑ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከር ድርሻዬን እወጣለሁ ብላለች። ዞኑ በሻምፒዮናው ያሸነፉትና የተሻለ ሰዓት ባስመዘገቡ 20 ስፖርተኞች ጥቅምት 25 ቀን 2011 በደብረ ታቦር ከተማ በሚካሄደው ክልል አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድር ይወከላል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም