ቀጥታ፡

ደጋፊ ያጡ ህፃናትን በማሳደግ ለቁም ነገር ለማብቃት የመላው ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ ጥቅምት 19/2011 ደጋፊ ያጡ ህፃናትን አሳድጎ ለቁም ነገር ለማብቃት በሚደረገው ጥረት የመላው ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ገለጸች። የቤተክርስቲያኗ የሕፃናትና ቤተሰብ ጉዳይ ድርጅት 45ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልን አስመልክቶ ከጥቅምት 10 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ሲያካሂድ የነበረውን ፕሮግራም በዛሬው እለት በፓናል ውይይትና በእውቅና መስጠት አጠናቋል። በመዝጊያው ላይ የተገኙት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ቀሲስ ሳምሶን በቀለ እንደገለጹት፤ ቤተክርስቲያኗ ደጋፊ ያጡና በጎዳና ተጥለው የተገኙ ህፃናትን አሳድጎ ለቁም ነገር ለማብቃት በመላው አገሪቷ የህፃናት ማሳደጊያ ማዕከላት አቋቁማ እየሰራች ትገኛለች። ቤተክርስቲያኗ በራሷ አቅምና በውጭ አገሮች በጎ አድራጊዎች ድጋፍ ላይ የተመሰረተ 36 የህጻናት ማሳደጊያ ማዕከል እንደነበራት ያስታወሱት ቀሲስ ሳምሶን የዓቅም ማነስ በማጋጠሙ የማዕከላቱ ቁጥር ወደ 17 ዝቅ ለማለት መገደዱን ገልጸዋል። የነበሩት የህፃናት ማሳደጊያ ማዕከላት ወደ ሥራ ተመልሰው ህፃናት መልካም ዜጋ ሆነው እንዲያድጉ ለማድረግ የራስን የሃብት ምንጭ በአገር ውስጥ ማጎልበት ያስፈልጋል። ስለሆነም በአገር ውስጥና በውጭ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባቸው ጠቅሰው ለዚህም አዲሱ የሲቪል ማኅበራት ረቂቅ ሕግ ምቹ መሆኑን ገልጸዋል። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመወያያ ርዕሰ ጉዳይ ያቀረቡት ዶክትር ፋንታሁን አድማሱ እንደጠቀሱት፤ በኢትዮጵያ ለችግር የተጋለጡ ህፃናት ቁጥር ከፍተኛ እንደሆነ ጠቅሰው ቤተክርስቲያኗ ህፃናትን የመርዳት ኃላፊነቷን መወጣት ይገባታል። በተለይ ቤተክርስቲያን የህፃናትን የመኖር፣ ከለላና ጥበቃ እንዲያገኙ፣ የእድገት ሁኔታቸው እንዳይስተጓጎሉና መብታቸው እንዲጠበቅ እያደረገች ያለውን ተግባር በስፋት መስራት ይኖርባታል። ይህም የህፃናቱ ጉልበት እንዳይበዘበዝ፣ ለህገ ወጥና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት እንዳይጋለጡ ለመከላከል የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል። ከሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር የተወከሉት አቶ ዳንኤል ፋንታሁን በበኩላቸው ማዕከላቱ የህፃናት የመኖር መብት፣ ጥቅማ ጥቅም፣ ደህንነት እንዲጠበቅና ከአድሎአዊ አሰራር የፀዱ እንዲሆን በተረጂ ህፃናት መረጣና በምልመላ ወቅት ህዝቡን ማሳተፍ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። ይህም ህፃናቱ የምግብ፣ የትምህርት፣ የጤና፣ የኢኮኖሚ፣ የስነ-ልቦናና ተጨማሪ ህጋዊ ከለላ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል ሲሉ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሕፃናትና ቤተሰብ ጉዳይ ድርጅት የዛሬ 45 ዓመት ከተመሰረተ ጀምሮ 40ሺህ ህፃናትን ተቀብሎ በማሳደግ ለቁም ነገር አብቅቷል። በኢትዮጵያ ወላጆቻቸውን ያጡ 4ነጥብ6 ሚሊዮን ህፃናት እንዳሉ መረጃዎች ያመለክታሉ።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም