በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ የሚሳተፉ የእጩዎች ዝርዝር ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ ግንቦት 14/2010 የአስመራጭ ኮሚቴው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ የሚወዳደሩ የእጩዎች ዝርዝር ይፋ አድርጓል። ኮሚቴው እስከ ግንቦት 11 ቀን 2010 ዓ.ም አጠቃላይ እጩ ተወዳዳሪዎችን ዝርዝር ተቀብሎ ተገቢነታቸውን አጣርቶ ዛሬ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ የሚሳተፉ የእጩዎች ዝርዝር አሳውቋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የፕሬዚዳንትና የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ምርጫ ግንቦት 26 ቀን 2010 ዓ.ም በአፋር ክልል ርዕሰ መዲና ሰመራ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል። አስመራጭ ኮሚቴው ይፋ ባደረገው የእጩዎች ዝርዝር መሰረት አቶ ጁነዲን ባሻህ ከድሬዳዋ፣ አቶ ተካ አስፋው ከአማራና አቶ ኢሳያስ ጂራ ከኦሮሚያ እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ለመሆን ይወዳደራሉ። በፕሬዚዳንት እጩነት ውስጥ የነበሩት አቶ ተስፋዬ ካህሳይ የወከላቸው የትግራይ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ውክልናቸውን ማንሳቱን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በደብዳቤ ማሳወቁን ተከትሎ በእጩነት አለመመረጣቸው ተገልጿል። በተጨማሪም የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ወክለው በፕሬዚዳንት እጩነት ቀርበው የነበሩት ኢንጂነር ፀደቀ ይሁኔ "የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያስቀመጣቸውን መስፈርቶች ባለማሟላታቸው" በእጩነት እንዳይካተቱ መደረጉን ኮሚቴው አስታውቋል። በፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንትነት ምርጫ ለመወዳደር የደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ወክለው የነበሩት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ባለፈው ሳምንት "በምርጫው ላይ ባለው ትርምስ ደስተኛ ስላልሆንኩ" በሚል ከምርጫው ራሳቸውን ማግለላቸው ይታወሳል። በተጨማሪም ኮሚቴው የዘጠኙ ክልሎችና የሁለቱ ከተማ መስተዳድሮች እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች የተወከሉ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ የሚወዳደሩ 22 እጩዎችን አሳውቋል። የቀድሞው የደደቢት ክለብ ፕሬዚዳንት ኮሎኔል አወል አብዱራሂም ከትግራይ፣ የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አቶ ሰውነት ቢሻው ከአማራ፣ አሰልጣኝ አስራት ሃይሌ ከአዲስ አበባ፣ አቶ አበበ ገላጋይ ከድሬዳዋና አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ ከደቡብ እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች በእጩነት ከቀረቡት ስራ አስፈጻሚ አባላት ውስጥ ይጠቀሳሉ። በእጩዎች ምርጫ ላይ ቅሬታ ያለው አካል ከግንቦት 15 እስከ 18 ቀን 2010 ዓ.ም በፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት በአካል በመቅረብ ቅሬታ ማቅረብ እንደሚችል የአስመራጭ ኮሚቴው ጠቁሟል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም