በመቀሌ ከተማ የ44 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የአስፖልት መንገድ ግንባታ ሊጀመር ነው

70
መቀሌ ጥቅምት 18/2011 የመቀሌ ከተማ አስተዳደር በተያዘው የበጀት ዓመት በ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወጪ የአስፖልት መንገድ ግንባታ ለማካሄድ የሚያስችለውን ስምምነት ከሱር ኮንስትራክሽን ጋር ዛሬ ተፈራረመ፡፡ ስምምነቱን የከተማው ምክትል ከንቲባ አቶ ብርሃነ ገብረእየሱስና የሱር ኮንስትራክሽን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ የማነ ፈርመዋል፡፡ ምክትል ከንቲባው አቶ ብርሃነ ገብረእየሱስ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ስምምነቱ የተካሄደው የከተማውን የንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማሳደግ በ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወጪ የ44 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ኮንክሪት የአስፖልት መንገድ ግንባታ ለማካሄድ ነው፡፡ ወሰን ማስከበር፣ የውሃና መብራት መስመሮች በስራው ላይ መጓተት እንዳያስከትል አስፈላጊው የካሳ ክፍያ ለማካሄድ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ቢሮዎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ የሚገነባው የአስፖልት መንገድ ወደ ከተማ የተከለሉ የገጠር ቀበሌዎች ጨምሮ ስድስት ክፍለ ከተማዎችን እርስ በርስ እንደሚያገናኝ ገልፀዋል፡፡ የሱር ኮንስትራክሽን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ የማነ በበኩላቸው የመንገድ ግንባታው ጥቅምት 19 ቀን 2011 ዓ.ም እንደሚጀመር ገልፀዋል፡፡ ከ20 እስከ 50 ሜትር ስፋት ያለውን ይህንኑ የአስፖልት መንገድ ግንባታ በሦስት ዓመት ጊዜ  ውስጥ ይጠናቀቃል፡፡ ለግንባታው አስፈላጊ የሆኑ ባለሙያዎች፣ የሰው ሃይል፣ ማሽነሪዎችና የኮንስትራክሽን እቃዎች መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም