በዩኒቨርሲቲው የተደረገልን አቀባበል ከጠበቅነው በላይ ነው-የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ አዲስ ገቢ ተማሪዎች፡፡ - ኢዜአ አማርኛ
በዩኒቨርሲቲው የተደረገልን አቀባበል ከጠበቅነው በላይ ነው-የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ አዲስ ገቢ ተማሪዎች፡፡

ሃረር ጥቅምት 18/2011 በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የተመደቡ አዲስ ገቢ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው የተደረገላቸው አቀባበል ከጠበቁት በላይ መሆኑን ገለጹ፡፡ ለዩኒቨርስቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትም የበኩላቸውን እንደሚወጡ አዲስ ገቢ ተማሪዎች አስታውቀዋል፡፡ የሐረማያ ዩኒቨርስቲ ለ2011 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የተመደቡለትን 4ሺ 622 አዲስ ገቢ ተማሪዎችን መቀበል የጀመረ ሲሆን አዲስ ገቢ ተማሪዎችም በዩኒቨርሲቲው መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች፣ በነባር ተማሪዎችና በአካባቢው ነዋሪዎች ደማቅ አቀባበል እየተደረገላቸው ነው፡፡ ወደ ሐረማያ ዩኒቨርስቲ በመግባት ላይ የሚገኙት አዲስ ገቢ ተማሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት በዩኒቨርስቲው የተደረገላው አቀባበል አስደሳችና ከጠበቁት በላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከደቡብ ክልል ሆሳዕና የመጣው ተማሪ አዱኛ አስፋው በዩኒቨርስቲው የተደረገለት አቀባበል እንዳስደሰተው ገልጾ "አቀባበሉ ወደ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ከመድረሴ በፊት ስሰማ የነበረው ትክክል ያልሆነ እና የታዛበ እንደነበር በተጨባጭ ማረጋገጥ አስችሎኛል" ብሏል። "የመጣሁት ለትምህርት እንደመሆኑ መጠን አላማዬን ለማሳካት ተዘጋጅቻለው ያለው ተማሪ አዱኛ በዩኒቨርስቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማር እንቅስቃሴ እንዲኖር የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተናግሯል፡፡ ከጋምቤላ ክልል የመጣችው ተማሪ ኢክራም መሐመድ በበኩሏ በዩኒቨርስቲው ማህበረሰብና በአካባቢው ነዋሪ የተደረገላቸው አቀባበል ከጠበቀችው በላይ መሆኑን ገልጻለች፡፡ "ለቤተሰቦቿ ሃሳብ አይግባችሁ" በማለት መልዕክቷን ያስተላለፈችው ተማሪ ኢክራም የዘንድሮውን የዩኒቨርስቲ ትምህርቷን ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንደምታጠናቅቅ እምነት እንዳላት ተናግራለች። ተማሪዎች ከአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተለያየ አስተሳሰብ፣ ቋንቋ፣ ባህልና ሐይማኖት ይዘን ወደ ዩኒቨርሲቲው መጥተናል ያለው ደግሞ ከአርሲ የመጣው ተማሪ ወንዶሰን ተስፋዬ ነው። ተማሪ ወንዶሰን አያይዞ እንደገለጸው "አዲስ ገቢ ተማሪዎችም ሆነ ነባር ተማሪዎች በመቻቻል፣ በመከባበርና በመደጋገፍ የመማር ማስተማሩን ሂደት ሰላማዊ በማድረግ የመጣንበትን ዓላማ ማሳካት ይገባል" ብሏል፡፡ ከዳውሮ ዞን የመጣው ተማሪ አላዛር ገዝሙ በበኩሉ በአቀባበሉ ደስተኛ መሆኑን ገልጾ "ወደ እዚህ የመጣሁበት አላማ መማርና መማር ብቻ ነው፣ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሰራን ለማሳካት የበኩሌን እወጣለው” ሲል ተናግሯል፡፡ በአዲስ ገቢ ተማሪዎች የአቀባበል ስነ ስርዓት ላይ የተገኙተ የአካባቢው ነዋሪ ወይዘሮ አለምጸሐይ ከድር አዲስ ገቢ ተማሪዎችን ከነባር ተማሪዎችና ከአካባቢው ወጣቶች ጋር በመሆን እየተቀበሉ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ተማሪዎችን በፍጹም ፍቅርና በባለቤትነት ስሜት እየተቀበሉ መሆኑን የተናገሩት ወይዘሮ አለምጸሐይ "የተማሪ ወላጅች ምንም ዓይነት ስጋት ሊገባቸው አይገባም" ብለዋል። የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ተወካይ ዶክተር ጀማል የሱፍ ከአካባቢው ማህበረሰብ፣ ከዩኒቨርስቲው መምህራንና አስተዳደር ሰራተኞች ጋር የትምህርት ዘመኑ የተሳካና ሰላማዊ እንዲሆን ውይይት ተደርጎ ከስምምነት መደረሱን አስታውሷል፡፡ አዲስ ገቢ ተማሪዎችን ከዩኒቨርስቲው 20 ኪሎ ሜትር እርቀት ድረስ በመሄድ አቀባበል እየተደረገ እንደሚገኝ የገለጹት ዶክተር ጀማል በመማር ማስተማርና በአገልግሎተ አሰጣጥ ዙሪያ ለግጭት መንስዔ ሊሆኑ የሚችሉ ክፍተቶች እንዳይፈጠሩ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን አዳዲስ ተማሪዎችን ጨምሮ 27ሺ የሚደርሱ ተማሪዎችን በመደበኛ፣በርቀት፣በተከታታይና በክረምት መርሃ ግብር ትምህርት ይሰጣል።