የርብ መስኖ ግድብ ፕሮጀክትን የቱሪስት መስህብ ማድረግ ይገባል -ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ - ኢዜአ አማርኛ
የርብ መስኖ ግድብ ፕሮጀክትን የቱሪስት መስህብ ማድረግ ይገባል -ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ

አዲስ አበባ ጥቅምት 18/2011 የርብ መስኖ ግድብ ፕሮጀክትን የቱሪስት መስህብ ለማድረግ መስራት እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አስገነዘቡ። በፕሮጀክቱ ምርቃት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት ፤ የርብ መስኖ ግድብ ፕሮጀክት ስራ ሲጀምር ለቱሪስቶች አዲስ ማሳያ እንደሚሆን ይጠበቃል። ጎንደር ብዙ ድንቅ ስፍራዎች ያሏት ታሪካዊ አካባቢ በመሆኗ ስፍራውን ቱሪስቶች እንዲጎበኙ፣ ልማት እንዲስፋፋና እድገት እንዲመጣ እያንዳንዱ አርሶ አደር በህይወቱ ለውጥ ማምጣት እንዲችል መረባረብ ያስፈልጋል ብለዋል። በአገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገትና ለውጥ ላይ ሳንታክት በመስራት ለሌሎችም መትረፍ አለብን ሲሉም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት። የርብ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክት ከ20 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የማልማት አቅም እንዳለውና ፕሮጀክቱ በአግባቡ በስራ ላይ ከዋለ ከ28 ሺህ በላይ በአካባቢው የሚኖሩ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተጠቁሟል። ከተንዳሆና ከሰም የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች በመቀጠል ከፍተኛ ውሃ የመያዝ አቅም ያለውና ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት የርብ የመስኖ ግድብ 800 ሜትር ርዝመትና ከመሰረቱ ጀምሮ የ99 ነጥብ 5 ሜትር ከፍታ አለው።