የርብ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክት ለዜጎች ዘላቂ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የሚፈጥር ነው- ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ - ኢዜአ አማርኛ
የርብ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክት ለዜጎች ዘላቂ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የሚፈጥር ነው- ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ
አዲስ አበባ ጥቅምት 18/2011 የርብ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክት በድህነት ውስጥ ላሉ አርሶ አደሮች ዘላቂ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የሚፈጥር መሆኑን የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ገለጹ። በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን የተገነባው የርብ ግድብ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በተገኙበት ተመርቋል። ኢንጂነር ስለሺ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት "ፕሮጀክቱ ከድህነት የሚያወጣ ብቻ ሳይሆን ሀብትና ጸጋም የሚፈጥር ነው"። ከ20 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የማልማት አቅም እንዳለውና በአግባቡ በስራ ላይ ከዋለ ከ28 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። በግድቡ የሚገኘው የውሃ ቋት ለአሳ እርባታ ስለሚጠቅም ለአካባቢው ነዋሪዎች ተጨማሪ የምግብና የገቢ ምንጭ በመሆን ጠቀሜታ እንደሚሰጠም ነው ሚኒስትሩ ያስረዱት። የግድቡ ፕሮጀክት በአካባቢው ለሚኖሩ ዜጎች የስራ እድል የፈጠረና በኢትዮጵያ በሚገኙ የተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች በመስኖ ልማት ለሚማሩ ተማሪዎች የተግባራዊ ስልጠና ልምድ ያገኙበት እንደሆነ ጠቅሰዋል። ይህ ፕሮጀክት በቀጣይ ዓመታት ለኢትዮጵያ አግሮ ኢንዱስትሪ የውጭ ምንዛሪ ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም አመልክተዋል። ፕሮጀክቱ ብዙ ችግሮችንና ውጣ ውረዶችን ያለፈ፣ መስዋዕትነት የተከፈለበትና ከባድ ፈተና የታየበት እንደሆነ ሊዘነጋ እንደማይገባና ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የልማት አቅም እንደሆነም ገልጸዋል። ፕሮጀክቱ የጎርፍ ችግርን ያቃለለና በቀጣይ በታችኛው ተፋሰስ ጎርፍን ለመቆጣጠርና የርብ ወንዝ ፍሰት ዓመቱን ሙሉ እንዲኖር ከማድረግ አንጻር ያለው ፋይዳ የጎላ ነው ብለዋል። ከግድቡ ፕሮጀክት የማስፈጸም አቅምን የማጎልበትና የመጨመር ልምድ እንደተገኘና እነዚህ ልምዶች በቀጣይ ግንባታቸው እየተካሄደ ላሉ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ለማጠናቀቅ እንደሚረዳም አስረድተዋል። በአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮች ግድቡ በጎርፍ ምክንያት ሊያጋጥመው የሚችለውን የደለል ክምችት ለመካለከል እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል። መንግስት በቀጣይ በመካከለኛና ሰፊ የመስኖ ልማት ስራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራም ጠቁመዋል። በአራት ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ በ2000 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው ርብ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክት ከተጠበቀው ጊዜ በላይ ዘግይቶ ዛሬ ተመርቋል። የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን የግድቡን ግንባታ ያካሄደ ሲሆን በዲዛይን ለውጥ፣ በኮንትራክተሩና አማካሪ ድርጅቶች የአቅም ውስንነትና ልምድ ማነስ ምክንያት ፕሮጀክቱ ይጠናቀቃል ተብሎ በታሰበበት ጊዜ ሊጠናቀቅ እንዳልቻለ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በተደጋጋሚ ጊዜ ሲገለጽ ቆይቷል። ሚኒስቴሩ የርብ መስኖ ግድብ ጥቅምት 25 ቀን 2010 ዓ.ም ይመረቃል ተብሎ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጹም የሚታወስ ነው። ርብ የመስኖ ግድብን በ2000 ዓ.ም በ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ለመገንባት ውል የተፈጸመ ቢሆንም፣ ግድቡ ሲጠናቀቅ 3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ፈጅቷል። ግድቡ 1 ሺህ ሔክታር ስፋትና 234 ሺህ ሜትር ኩብ ውሃ የሚይዝ ሲሆን ይህም ከተንዳሆና ከሰም የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች በመቀጠል ከፍተኛ ውሃ የመያዝ አቅም ያለው ነው። ከ800 ሜትር ርዝመትና ከመሰረቱ ጀምሮ የ99 ነጥብ 5 ሜትር ከፍታም አለው። በአሁኑ ወቅት ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተገነቡ የሚገኙት የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ በኢትዮጵያ የመስኖ እንቅስቃሴ ላይ ጉልህ ለውጥ ያመጣሉ ተብሎይጠበቃል። ያም ቢሆን ፕሮጀክቶቹ መጠናቀቅ በነበረባቸው ጊዜ አለመጠናቀቃቸው በስፋት የሚታይ ችግር ከመሆኑ በተጨማሪ የፕሮጀክቶቹ መጓተት ኢትዮጵያን ከፍተኛ ወጪ እያስወጣት ይገኛል።