ቀጥታ፡

በጌዴኦ ዞን በተያዘው በጀት ዓመት 27 ሺህ ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ ነው

ዲላ ጥቅምት18/2011 በጌዴኦ ዞን በተያዘው በጀት ዓመት 27 ሺህ ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ መታቀዱን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ አስታወቀ፡፡ ከታቀደው የቡና መጠን 85 በመቶው ደረጃ አንድ እና ሁለት እንዲሆን ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው፡፡ የጌዴኦ ዞን እርሻ እና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ ምክትል ኃላፊና  እና የቡናና ሻይ ቅመማ-ቅመም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አድማሱ ተፈራ ለኢዜአ እንደገለጹት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ የታቀደውን ቡና ለማሳካት የመጀመሪያ ደረጃ የግብይት ማዕከላትን የማጠናከርና ሕገ-ወጥ የቡና ዝውውር ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ ነው፡፡ ከዞን እስከ ቀበሌ መዋቅር ድረስ የቡና ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ መገባቱን ገልፀዋል፡፡ ባለፈው አመት ለማዕከላዊ ገበያ ከቀረበው ቡና 80 በመቶው ደረጃ አንድና ደረጃ ሁለት እንደነበር ያስታወሱት በተያዘው በጀት አመት ደረጃ አንድና ደረጃ ሁለት የቡና መጠኑን ወደ 85 በመቶ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዞኑ ቡና አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች በአብዛኛው የእሸት ቡና ግብይት መጀመሩን የጠቆሙት አቶ አድማሱ ለማዕከላዊ ገበያ የሚቀርበው የታጠበ ቡና ጥራቱን ጠብቆ እንዲቀረብ ለአርሶ አደሩና ኢንዱስትሪዎች ክትትልና ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ለአርሶ አደሮችና ለ140 የእሸት ቡና መፈልፈያ ኢንደስትሪ ኃላፊዎች ስለ ቡና ምርት አሰባሰብ፣ አዘገጃጀትና ጥራት አጠባበቅ የግናዛቤ ማስጨበጫ ሙያዊ ሥልጠና መሰጠቱን አስታውቀዋል፡፡ በጌዴኦ ዞን ኮቾሬ ወረዳ የሀማ የታጠበ ቡና ማዘጋጃ ኢንዱስትሪ ኃላፊ አቶ አበበ መንግስቱ እሸት ቡና ወደ ኢንደስትሪው ሲገባ ከባዕድ ነገር ጋር አለመቀላቀሉ ተረጋግጦ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ቡናው ለማዕከላዊ ገበያ እስኪቀርብ ድረስ በኢንዱስትሪ ውስጥ የጥራት ደረጃ ሂደቱን እንዲጠብቅ የቴክኒክ ቁጥጥር ሥራ እንደሚያከናውኑ አስረድተዋል፡፡ በወናጎ ወረዳ ሞኮኒሳ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ሞዴል አርሶ አደር ዘለሉ አራርሶ እንደተናገሩት ስድስት ሄክታር በሚሆን የቡና እርሻ የሚያመርቱትን ቡና ባላቸው አነስተኛ የእሸት ቡና መፈልፈያ ማሽን ጥራቱን ጠብቀው በማዘጋጀት ለገበያ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል፡፡ በሄክታር በአማካይ 16 ኩንታል ቡና እንደሚያመርቱ ያስታወቁ አርሶ አደሩ በባለፈው አመት የብስለት ደረጃውን ጠብቀው የሰበሰቡትን እሸት ቡና በማዘጋጀት አንድ ሺህ ኪሎ ግራም ቡና  ለውጭ ገበያ አቅርበው ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ ’’ዘንድሮ የተሻለ ምርት እሰበስባለሁ የሚል እምነት አለኝ’’ ያሉት አርሶ አደሩ ከአምናው የተሻለ ቡና ለገበያ ለማቅረብ ማቀዳቸውን ተናግረዋል፡፡ የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ማርቆስ አሰፋ በበኩላቸው ከባለፈው አመት ምርታቸው ሁለት ሺህ ኪሎ ግራም እሸት ቡና በአካባቢያቸው ለሚገኝ ኢንዲስትሪ ማቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡ ዘንድሮ ከአምናው የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ የገለፁት አርሶ አደሩ የቀላና ጊዜው ያላለፈበትን እሸት ቡና ለኢንዱስትሪዎች እንደሚያቀርቡ አስረድተዋል፡፡ በጌዴኦ ዞን በተያዘው የምርት ዘመን ከ103 ሺህ ቶን በላይ ቡና እንደሚሰበሰብና 205 የታጠበና ያልታጠበ ቡና የሚያዘጋጁ ኢንደስትሪዎች ወደ ስራ እንደሚገቡ ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም