በገቢዎችና ጉምሩክ መስሪያ ቤት ያለውን የሰው ኃይል በመጠቀም የመንግስትን ገቢ ማጠናከር ይቻላል - ወይዘሮ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
በገቢዎችና ጉምሩክ መስሪያ ቤት ያለውን የሰው ኃይል በመጠቀም የመንግስትን ገቢ ማጠናከር ይቻላል - ወይዘሮ አዳነች አቤቤ
ደብረዘይት ጥቅምት 18/2011 በገቢዎችና ጉምሩክ መስሪያ ቤት በአሁኑ ወቅት ያለውን የሰው ኃይልና እውቀት በመጠቀም የመንግስትን ገቢ ማጠናከር ይቻላል ሲሉ ሚኒስትሯ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ገለፁ። መስሪያ ቤቱ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ የሚወጡትን አንደሚሸልም፤ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በማይወጡት ላይ ደርሞ እርምጃ እንደሚወሰድም ሚኒስትሯ አስጠንቅቀዋል። የገቢዎችና ጉምሩክ ሚኒስቴር ሰራተኞች የተያዘው ዓመት የመጀመሪያ ሶስት ወራት እቅድ አፈጻጸምና ቀጣይ ስራዎች ላይ በቢሾፍቱ ዛሬ ውይይት ጀምረዋል። ሚኒስትሯ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት "በአሁኑ ወቅት በመስሪያ ቤቱ ያለውን የሰው ኃይል እውቀት በቁርጠኝነተ መጠቀም ከተቻለ በገቢዎችና ጉምሩክ ላይ የሚታዩ ክፈተቶችን ቀርፎ አገሪቱ ማሳካት የምትፈልገውን ለውጥ ማምጣት ይቻላል፤" በመጪዎቹ መቶ ቀናት ውስጥ ዘርፉ የሚፈለገውን ግብ ለማሳካት ተጨማሪ እቅዶች ላይ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ጠቅሰዋል። እነዚህን ዓላማዎች ለማሳካት ደግሞ በቂ የሰው ሃይል እንዳለ የገለጹት ሚኒስትሯ አቀናጅቶ መስራት ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አስታውቀዋል። ስራዎቹ የሚለኩት በሚመዘገቡ ለውጦች ብቻ እንደሚሆንም ነው ወይዘሮ አዳነች የተናገሩት። "የተዋጣለት ሥራ ለማስመዝገብ የሚሰሩትን ማበረታታትና መሸለም እንዲሁም በአፈጻጸማቸው ችግር ያለባቸውን ደግሞ ተጠያቂ ማድረግ፤ ለስራው እንቅፋት በሚሆኑበት ጊዜም የማሰናበት እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል። ውይይቱ ዛሬን ጨምሮ ለተከታታይ ሶሰት ቀናት የሚቆይ ሲሆን ከየቅርንጫፎቹ ሪፖርቶች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል።