ማኑዌል ቫዝ ፒንቶ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ተለያዩ - ኢዜአ አማርኛ
ማኑዌል ቫዝ ፒንቶ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ተለያዩ
አዲስ አበባ ጥቅምት 18/2011 ፓርቹጋላዊው የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ ካርሎስ ማኑዌል ቫዝ ፒንቶ ክለቡን መልቀቃቸው ተገለጸ። አሰልጣኙ የአንድ ዓመት ውል ቢቀራቸውም ከክለቡ ጋር በስምምነት መለያየታቸውን የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ምኒልክ ግርማ ለኢዜአ ገልጸዋል። ቫዝ ፒንቶ በክለቡ ስለነበራቸው ቆይታ ማህበሩ ምስጋና ማቅረቡንም ተናግረዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ የቀድሞ አሰልጣኙ ኔዘርላንዳዊው ማርት ኑይ በገጠማቸው የጤና እክል ክለቡን መልቀቃቸውን ተከትሎ ፖርቱጋላዊውን ካርሎስ ማኑኤል ቫዝ ፒንቶን መስከረም 2010 ዓ.ም አሰልጣኙ አድርጎ መሾሙ የሚታወስ ነው። አሰልጣኙ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የኢትዮጵያ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ባለቤት ሲሆኑ ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ እንዲያጠናቅቅ አድርገዋል። በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግና በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅዱስ ጊዮርጊስ ስኬታማ ጊዜን ባያሳልፍም የ44 ዓመቱ አሰልጣኝ ክለቡን በአህጉራዊው የውድድር መድረክ ላይ መርተዋል። ማኑኤል ቫዝ ፒንቶ ከቅዱስ ጊዮርጊስ በፊት የአንጎላዎቹን ሪክሬቲቮ ዲቦሎና ሪክሬቲቮ ዲ ካላን አሰልጥነዋል። ብራዚላዊው ኔይደር ዶስ ሳንቶስ፣ሆላንዳዊ አሰልጣኝ ሬኔ ፌለር፣ጀርመናዊ ሚሼል ክሩገር፣ ሰርቢያዊው ሚሉቴን ሰርዶቪች ሙሉቲን "ሚቾ"፣ ሆላንዳዊው ሀንስ ቫንደር ፕሊዩም፣ ኢጣልያዊያኑ ጂዮሴፔ ዶሴና ፒዬር ሉዊጂ ዳንኤሎና ሆላንዳዊው ማርት ኖይ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከዚህ በፊት ያሰለጠኑ የውጭ አገር አሰልጣኞች ናቸው።