ዓመታዊው የወርልድ ቴኳንዶ የግል የበላይነት ሻምፒዮና መካሄዱ እንደቀጠለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዓመታዊው የወርልድ ቴኳንዶ የግል የበላይነት ሻምፒዮና መካሄዱ እንደቀጠለ ነው
አዲስ አበባ ጥቅምት 18/2011 ዓመታዊው የወርልድ ቴኳንዶ የግል የበላይነት ሻምፒዮና መካሄዱን እንደቀጠለ ነው። ውድድሩ ትናንት ቀጥሎ ሲውል በሴቶች 49 ኪሎ ግራም እና በወንዶች 54 ኪሎ ግራም የፍጻሜ ጨዋታ ተካሂዷል። በዚሁ መሰረት በ49 ኪሎ ግራም ሴቶች ሶፊያ በለጠ ውብዓለም በየነን በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያ ስታገኝ ውብዓለም የብር ሜዳሊያ ባለቤት መሆኗን የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ዳዊት አስፋው ለኢዜአ ገልጸዋል። በ49 ኪሎ ግራም የተወዳደሩት ነጃት አባይነህና ቃልኪዳን ወርቁ ያገኙት ነጥብ ተመሳሳይ በመሆኑ የነሐስ ሜዳሊያ ማግኘታቸውን ተናግረዋል። በወንዶች 45 ኪሎ ግራም ቢኒያም ጥላሁን ተስፋዬ ባንቲን በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘ ሲሆን ተስፋዬ የብር ሜዳሊያ ባለቤት ሆኗል። አቤኔዘር ሙሉጌታና ዮሴፍ አያና ባደረጉት ጨዋታ ተመሳሳይ ነጥብ በማግኘታቸው ሁለቱም የነሐስ ሜዳሊያ ማግኘታቸውን ፕሬዝዳንቱ ጠቅሰዋል። ከአንድ እስከ ሶስት ለሚወጡ ተወዳዳሪዎች በቅደም ተከትል የ10፣ የአምስት እና ሶስት ሺህ ብር ሽልማት እንደሚበረከትላቸውም ነው አቶ ዳዊት ያስረዱት። ዛሬም ሻምፒዮናው ሲቀጥል በወንዶች 63 ኪሎ ግራምና በሴቶች 53 እና 62 ኪሎ ግራም የፍጻሜ ጨዋታዎች እንደሚካሄዱም ጠቁመዋል። በወርልድ ቴኳንዶ ብቁና ጠንካራ ተወዳዳሪ በማፍራት ኢትዮጵያን በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያስጠሩ ስፖርተኞችን መመልመልና ለታዳጊ ወጣቶች የውድድር አማራጭ ማስፋት የሻምፒዮናው ዓላማ እንደሆነም ጠቅሰዋል። ዓመታዊው የወርልድ ቴኳንዶ የግል የበላይነት ሻምፒዮና በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ነገ ፍጻሜውን ያገኛል።