በፕሪሚየር ሊጉ የዛሬ ጨዋታዎች አዳማ ከተማ ጅማ አባ ጅፋርን ያስተናግዳል - ኢዜአ አማርኛ
በፕሪሚየር ሊጉ የዛሬ ጨዋታዎች አዳማ ከተማ ጅማ አባ ጅፋርን ያስተናግዳል
አዲስ አበባ ጥቅምት 18/2011 የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬም ሲቀጥሉ አዳማ ከተማ የአምናውን የሊጉ አሸናፊ ጅማ አባ ጅፋርን ያስተናግዳል። ትናንት የተጀመረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬም በክልል ከተሞችን በአዲስ አበባ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይቀጥላል። በሲሳይ አብርሃም የሚሰለጥነው አዳማ ከተማ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት የአምናውን የሊጉ አሸናፊ ጅማ አባ ጅፋርን ያስተናግዳል። ሁለቱ ክለቦች በባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በተገናኙበት ወቅት ጅማ አባ ጅፋር አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ አቻ ወጥተዋል። በተለይም ባለፈው ዓመት ፕሪሚየር ሊግ የ30ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ በጅማ ስታዲየም ጅማ አባ ጅፋር አዳማ ከተማን አምስት ለ ዜሮ በማሸነፍ የሊጉ ሻምፒዮን መሆኑን ያረጋገጠበት ጨዋታ እንደነበር አይዘነጋም። ጅማ አባ ጅፋር የባለፈውን ዓመት ክብሩን ለማስጠበቅ የሚያደርገውን ጨዋታ ለማሸነፍ እንዲሁም አዳማ ከተማ የውድድር ዓመቱን በድል ለመጀመር የሚያደርጉት ጨዋታ በእግር ኳስ አፍቃሪው ዘንድ ተጠባቂ ሆኗል። ሌሎች በክልል ከተሞች በሚደረጉ ጨዋታዎች በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም በክለቡ ላይ የስያሜ ለውጥ ያደረገው መቐለ ሰብዓ እንደርታ (በቀድሞው መጠሪያ መቐለ ከተማ) ከደደቢትና በሀዋሳ አርቴፊሻል ስታዲየም ሀዋሳ ከተማ ከወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲ በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ይጫወታሉ። በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 10 ሰዓት ኢትዮጵያ ቡና ድሬዳዋ ከተማን ያስተናግዳል። ትናንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሲጀመር በሃዋሳ አርቴፊሻል ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ሲዳማ ቡና በፀጋዬ ባልቻና በአዲስ ግደይ ፋሲል ከተማን ሁለት ለ አንድ በሆነ ውጤት ማሸነፉ የሚታወስ ነው። ናይጄሪያዊው አጥቂ ኢዙካ ኢዙ ለፋሲል ከተማ ብቸኛውን ጎል አስቆጥሯል። በዚሁ መሰረት ፀጋዬ ባልቻ የፕሪሚየር ሊጉን የመጀመሪያ ጎል ሲያስቆጠር የፋሲል ከተማው ሙጂብ ቃሲም የሊጉን የመጀመሪያ ቢጫ ካርድ ተመልክቷል። የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 22ኛው የውድድር ዓመት ነው።