የእግረኛ መንገዶችን መልሶ የመገንባት ስራው ፈጥኖ እንዲጠናቀቅ ነዋሪዎች ጠየቁ

51
አዲስ አበባ ግንቦት 14/2010 የእግረኛ መንገዶችን መልሶ የመገንባት ስራ ፈጥኖ ቢጠናቀቅ ከክረምቱ ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችል አደጋን ለመከላከልና የትራፊክ ፍሰቱን ሰላማዊ ለማድረግ እንደሚያግዝ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ተናገሩ። የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን በበኩሉ ቀደም ብለው የተጀመሩ የእግረኛ መንገዶችን በዚህ ወር በማጠናቀቅ ለህብረተሰቡ ምቹ እንደሚያደርግ ገልጿል። በተለያዩ ክፍለ ከተሞች በመልሶ ጥገና የእግረኛ መንገዶች በመገንባት ለእግረኛው ምቹ እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑንም ነዋሪዎቹ ይናገራሉ። ይሁንና መልሶ የመጠገን ስራው ክረምቱ ከመጠንከሩ በፊት ቢጠናቀቅ እግረኛው ራሱን ከአደጋ እንዲጠብቅ ከማድረጉ ባሻገር ለአሽከርከሪው ምቹ ይሆናል ይላሉ። በተጨማሪም የተቆፈሩ ጉድጓዶች ነዋሪውን አደጋ ላይ እየጣሉ በመሆኑ ይህም ከክረምት በፊት ቢታሰብበት ሲሉ ጠይቀዋል። በአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የማዕከላዊ አዲስ አበባ የመንገድ ኃብት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ በላይ ወልደአረጋይ እንደገለጹት፤ የተጀመረው የእግረኛ መንገድ መልሶ የመጠገን ስራ በዚህ ወር ይጠናቀቃል። ከተጀመሩት ውስጥ በስድት ኪሎ፣ አራት ኪሎና ፒያሳ አካባቢ ያሉት ክረምት ከመግባቱ በፊት ሙሉ ለሙሉ ተጠናቀው ለህብረተሰቡ ምቹ ይሆናሉ ብለዋል ።  የእግረኛውን መንገድ ጥገና ከመስራት ባለፈ በስፋት እየተሰራ ያለው ለተለያዩ ስራዎች የተከፈቱ ትቦችን እንደሚከደኑም ገልጸዋል። ባለስልጣኑ በቀጣይም ባልተዳረሱ ክፍለ ከተሞች የእግረኛ መንገድ መልሶ የመጠገንና አዳዲሶችን እንደሚሰራ ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም