የትግራይ ልማት ማህበር 11ኛ ጉባኤውን ሊያካሂድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የትግራይ ልማት ማህበር 11ኛ ጉባኤውን ሊያካሂድ ነው

መቀሌ ጥቅምት 18/2011 የትግራይ ልማት ማህበር 11ኛ መደበኛ ጉባኤውን ከጥቅምት 24 ቀን 2011 ጀምሮ በመቀሌ ከተማ እንደሚያካሂድ አስታወቀ፡፡ ጉባኤው ''ጉባኤያችን የአንድነታችን መሰረትና መጪው ብሩህ ተስፋ ነው'' በሚል መሪ ቃል እንደሚካሄድ የማህበሩ ቦርድ ሰብሳቢ ኘሮፌሰር ክንደያ ገብረሂወት ገልፀዋል፡፡ በጉባኤው ባለፉት ዓመታት ማህበሩ ያከናወናቸውን ተግባራት የሚገመገመ ከመሆኑም በላይ በቀጣይ ሶስት ዓመታት ሊሰሩ የታቀዱና በሳይንስና ቴክኖሎጂ ላይ ያተኮሩ ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግ አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ እንደሚጠቅ አስታውቀዋል። የትግራይ ልማት ማህበር ዋና ዳይሬክተር ደክተር ታደለ ሀጎስ በበኩላቸው ባላፉት ሶስት ዓመታት ከማህበሩ አባላትና ደጋፊዎች በተገኘ ከ552 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ በክልሉ የተለያዩ የልማት ስራዎች መከናወናቸውን ገልፀዋል፡፡ በተገኘው የገንዘብ ድጋፍ ከተከናወኑ የልማት ስራዎች መካከል የዘጠኝ ትምህርት ቤቶች ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት በመስጠት ላይ ሲሆኑ የሌሎች ሦስት ትምህርት ቤቶች ግንባታም በመካሄድ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም 16 የሳይንስና ቴክኖሎጂ ማእከላት ግንባታ በመፋጠን ላይ መሆኑንም አመላክተዋ፡፡ በክልሉ ለሚገኙ በርካታ ጤና ተቋማትም ማህበሩ የመድሃኒትና የህክምና መሳሪያዎች ድጋፍ እንዲያገኙ መስራቱን አስታውቀዋል፡፡ በተጠቀሱ ተቋማት ግንባታ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚበልጡ የማህበሩ አባላት ገንዘብ በማዋጣት ቁልፍ ሚና መጫወታቸውን ገልፀዋል። በመቀሌ ለሁለት ቀናት በሚካሄደው የማህበሩ 11ኛ ጉባኤ ከመላ ዓለምና ከአገር ውስጥ የተውጣጡ አንድ ሺህ የጉባኤ አባላት በድምፅ እንደሚሳተፉ ለማወቅ ተችሏል።