ቀጥታ፡

ኦብነግ በሰላማዊ መንገድ ትግሉን ለመቀጠል ያደረገውን ስምምነት እንደግፋለን...የደገሐቡር ነዋሪዎች

ጅጅጋ ጥቅምት 17/2011  የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) ከመንግስት ጋር በሰላም ለመስራት በመስማማቱ በሶማሌ ክልል የደገሃቡር ነዋሪዎች ድጋፋቸውን በሰላማዊ ሰልፍ ገለጹ። ስምምነቱ የአከባቢውን ሰላም ለማረጋገጥ እንደሚያስችል ነዋሪዎቹ ተናግረዋል። ሰልፈኞቹ የኢፌዴሪና የክልሉን ሰንደቅ ዓላማዎች እንዲሁም የግንባሩን ዓርማ በማውለብለብ በከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች በመዘዋወር ስምምነቱን እንደሚደግፉ አረጋግጠዋል፡፡ በአሥመራ ከተማ በቅርቡ ለተደረሰው የሰላም ስምምነት ተግባራዊነት የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል፡፡ ከሰልፈኞቹ መካከል አቶ አህመድ መሐመድ ግንባሩ ከመንግሥት ጋር ያደረገው ስምምነት የህዝቡን የሰላምና የልማት ጥያቄ መሠረት ያደረገ ነው የሚል እምነት አለኝ ብለዋል፡፡ ''ከጦርነት የሚገኝ ትርፍ አይኖርም። ድርጅቱ የሰላም አማራጭ ይከተላል የሚል ተስፋ ነበረኝ'' ያሉት አቶ አህመድ፣ ''ግንባሩ ዓላማውን በሰላማዊ መንገድ ብቻ ለማካሄድ መወሰኑ እንደ ትልቅ ድል ነው የማየው'' ሲሉም ተናግረዋል ፡፡ ወጣት ኢልሃን ሐሰን በበኩሉ ''ስምምነቱ የተለየ እፎይታ ፈጥሮብኛል ግንባሩ ከዚህ በፊት የሚከተለውን የጦርነት አማራጭ በመተው አገራዊ ለውጡን ለመደገፍ የሰላም ስምምነት ማድረጉ የአከባቢውን ህዝብ አንድነት ለማጠናከር ይረዳል'' በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ ''የግንባሩን ዓርማ እንኳን በአደባባይ መያዝ ቀርቶ ስሙን መጥራት እንደወንጀል ነበር የሚቆጠረው'' ያለው አስተያየት ሰጪው ወጣት፣ለውጡን በሃገሪቱና በክልሉ ላመጡት መሪዎች ምስጋናውን አቅርቧል። የደገሃቡር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መሐመድ ሐሰን እንዳሉት የከተማው ህዝብ በራሱ ተነሳሽነት ስምምነቱን በመደገፍ ሰልፍ መውጣቱ ለሰላም የሰጠውን ዋጋ ያመለክታል ብለዋል። በምርጫ ጊዜም የሚፈልገውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ  ዕድል እንደሚሰጠው ገልጸው ይሄም የክልሉን የተፈጥሮ ሀብት እኩል ለመጠቀምና የሕዝቡን ሕይወት ለመለወጥ የራሱ አስተዋፅኦ እንዳለውም ከንቲባው አስታውቀዋል፡፡ ሕዝብ ስምምነቱን ተጠቅሞ የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ የክልሉንና የከተማ አስተዳደር አመራሮች የጀመሩትን የለውጥ እርምጃ እንዲደግፍም አሳስበዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትና ኦብነግ የሰላም ሰምምነቱን የተፈራረሙት ጥቅምት 11 ቀን 2011 ሲሆን ይሄም ከ30 ዓመታት በላይ የቆየውን ግጭት ለማስወገድ ያስችላል ተብሎም ታምኖበታል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም