ቀጥታ፡

የአፍሪካ ቀንድ የሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ተመሰረተ

አዲስ አበባ ጥቅምት 17/2011 የአፍሪካ ቀንድ አገሮች የሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽኖች ለሁለት ቀናት ባካሄዱት ጉባኤ 'የአፍሪካ ቀንድ የሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን' መመስረታቸውን ይፋ አድርገዋል። የኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ጂቡቲ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ኬንያ  እና የኡጋንዳን የሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽኖችን የኮንፌዴሬሽኑ መስራች አባላት ናቸው። ኮንፌዴሬሽኑ የሚተዳደርበት ደንብ ጸድቆ ከሁሉም አባል አገሮች አባል የተካተተበት የኮንፌዴሬሽኑ የቦርድ አባላትና አመራሮች ተመርጠዋል። የኤርትራ ሰራተኞች ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ተከሰተ ባይረ የምስራቅ አፍሪካ የሰራተኛ ኮንፌዴሬሽን እንዲመሩ በፕሬዚዳንትነት ተመርጠዋል። የኢትዮጵያ ሰራተኞች ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሌ የኮንፌዴሬሽኑ ዋና ፀሐፊ ሆነዋል። የኮንፌዴሬሽኑ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ እንዲሆን መወሰኑን ተከትሎ የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ኦሎምፒያ አካባቢ ከሚገኘው ዋና መስሪያ ቤቱ ቢሮ ለመስጠት ቃል ገብቷል። ኮንፌዴሬሽኑ በፋይናንስ አቅም ጥገኛ እንዳይሆን እያንዳንዱ የኮንፌዴሬሽኑ አባል ከ2ሺህ ዶላር ጀምሮ አቅሙ እስከሚፈቅደው ድረስ መዋጮ እንዲያደርግ በመተዳደሪያ ደንቡ እንዲደነገግ አባል አገሮቹ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል። የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ተከስተ ባይረ እንደገለፁት፤ የኮንፌዴሬሽኑ መመስረት የሰራተኞችን መብት ለማስከበርና የልምድድ ልውውጦች ለማድረግ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል። ለአፍሪካ ቀንድ አገሮች ሰራተኞች የተሻለ የሥራ ሁኔታ ለመፍጠር ጥሩ ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል። በኮንፌዴሬሽኑ አባላት መካከል የአቅም ግንባታ፣ የቴክኒክና የዕውቀት ችግሮችን በጋራ ታግሎ ለመሙላት የሚሰሩ መሆኑን አቶ ተከስተ ገልጸዋል። የኮንፌዴሬሽኑ ዋና ፀሐፊ ሆነው የተመረጡት አቶ ካሳሁን ፎሌ በበኩላቸው የአፍሪካ ቀንድ ሰራተኞች መብታቸውና ጥቅማቸው ተጠብቆ ለአካባቢው ዕድገትና ብልፅግና ሚና እንዲጫወቱ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል። ''በአፍሪካ ቀንድ የህግ የበላይነት እንዲከበርና ዴሞክራሲ እንዲያብብ እንዲሁም ስደትን ለማቆም በጋራ ኮንፌዴሬሽኑን አጠናክሮ መስራት አለብን'' ብለዋል። ከአፍሪካ ቀንድ መንግስታት በመሆንም የሰራተኞች ኑሮ ለማሻሻልና የሚያጋጥሙ ችግሮች እንዲፈቱ በመቀራረብ የሚሰራበት ሁኔታ እንደሚፈጠር አቶ ካሳሁን ተናግረዋል። በቀንዱ አገሮች የተመሰረተው ኮንፌዴሬሽን ሁሉንም የምስራቅ አፍሪካ አገሮች ያካተተና ጠንካራ እንዲሆን እንደሚሰራም ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም