ቀጥታ፡

የትምህርት ቤቱ ክፍያ አቅማችንን ያገናዘበ አይደለም... የተማሪ ወላጆች

ሶዶ ጥቅምት 17/2011 በወላይታ ሶዶ ከተማ የሚገኘው አባ ፓስካል የልጃገረዶች ትምህርት ቤት ክፍያ አቅማችንን ያላገናዘበና ያልተወያየንበት ነው ሲሉ የተማሪ ወላጆች ቅሬታቸውን ገለጹ፡፡ ትምህርት ቤቱ በበኩሉ የተለያዩ ግንባታዎችን ለማካሄድና የመምህራን ደመወዝ ጭማሪን ታሳቢ በማድረግ ነው ጭማሪ ያደረኩት ቢልም መምህራኑ የደመውዝ ጭማሪ አልተደረገልንም ብለዋል፡፡ በሶዶ ከተማ የመርካቶ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ህሊና ዘማች በትምህርት ቤቱ ለሚያስተምሯት ልጃቸው የሚከፍሉት ገንዘብ ትምህርት ቤቱ ከተቋቋመበት ዓላማ አንጻር ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ "ባለፈው ዓመት 250 ብር የነበረው ወርሀዊ የትምህርት ክፍያ ትምህርት ቤቱ ከእኛጋ ውይይት ሳያደርግ ዘንድሮ ወደ 300 ብር ማሳደጉና ለምዝገባ በሚል ተጨማሪ 100 ብር ማስከፈሉ አቅምን ያላገናዘበና ተገቢነት የሌለው ነው" ብለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በትምህርት ቤቱ የትምህርት ጥራት በየጊዜው እየቀነሰ በመምጣቱ ተገቢ ትኩረት ሰጥቶ ማስተካከል እንደሚገባ ነው ወይዘሮ ህሊና የገለጹት፡፡ "ቀደም ሲል ነጻ አገልግሎት ይሰጥ የነበረው ትምህርት ቤት ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ በየዓመቱ አቅማችንን ያላገናዘበ የዋጋ ጭማሪ ማድረጉ አግባብ ስላልሆነ ሊስተካከል ይገባል" ያሉት ደግሞ አቶ ደሳለኝ ዋዳ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ናቸው፡፡ ትምህርት ቤቱ የተሻለ አቅም ያላቸው መምህራንን መቅጠር ባለመቻሉ በልጆቻቸው ትምህርት ላይ ክፍተት አይተው በተደጋጋሚ ለትምህርት ቤቱ ማሳወቃቸውን አስታውሰው፣ መንግስት ጣልቃ ገብቶ ለሚስተዋሉ ችግሮች መፍትሄ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡ አቶ ጌታሁን ጃቤ የተባሉ የትምህርት ቤቱ መምህር በበኩላቸው ከሰባት ዓመት በላይ በትምህርት ቤቱ ማገልግላቸውንና ላለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት የደመወዝ ጭማሪና ጥቅማ ጥቅም ክፍያ ባልታወቀ ምክንያት በትምህርት ቤቱ መቋረጡን ተናግረዋል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ከመንግስት ትምህርት ቤቶች ጋር ይደረጉ የነበሩ የልምድ ልውውጦችና ስልጠናዎች መቋረጣቸው በትምህርት ቤቱ ለትምህርት ጥራት መጓደል አስተዋጽኦ እያደረገ በመሆኑም መንግስት ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል፡፡ የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አባ ብርሃኑ ወልዕማጎ በበኩላቸው ትምህርት ቤቱ ከዚህ ቀደም ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ይደረግለት የነበረው ድጋፍ መቆሙን ገልጸዋል። የመምህራን ደመወዝ ለመጨመርና በ3 ሚሊዮን ብር በትምህርት ቤቱ ግንባታቸው እየተካሄደ ላለው ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች ገቢ ለማግኘት ሲባል በትምህርት ክፍያ ላይ ጭማሪ መደረጉን አስረድተዋል፡፡ ከማህበረሰቡ ጋር ውይይትና መግባባት ላይ ሳይደረስ በወራዊ የትምህርት ክፍያ ላይ ጭማሪ መደረጉ አግባብ እንዳልሆነ አምነው በቀጣይ የተማሪ ወላጆችን ለማወያየት መድረክ እንደሚያዘጋጅ ገልጸዋል፡፡ "የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ፣ የመምህራንን የደመወዝ ጭማሪና ጥቅማ ጥቅም ጥያቄ ለመመለስ ትምህርት ቤቱ በትኩረት ይሰራል" ብለዋል፡፡ የወላይታ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ተፈሪ ላብሶ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርሲቲያን ለማህበረሰቡ ከምትሰጣቸው ማህበራዊ አገልግሎቶች ትምህርት አንዱ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ ትምህርት ቤቱ ቀደም ብሎ ወላጆችን ሳያወያይና በጋራ መግባባት ላይ ሳይደርስ በትምህርት ክፍያ ላይ ጭማሪ ማድረጉ አግባብነት እንደሌለው አስታውቀዋል። ከመምህራን ጥቅማ ጥቅም ጋር በተያያዘ እየተነሳ ያለው ቅሬታን ለማጣራትም በመምሪያው በኩል ኮሚቴ ተቋቁሞ የማጣራት ሥራ እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡ " እንደ ዞን የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ልዩ ትኩረት በመስጠቱ ክፍተቶችን ነቅሰን በማውጣት በተደራጀ መልኩ ምላሽ እንሰጣለን " ብለዋል፡፡ አባ ፓስካል የልጃገረዶች ትምህርት ቤትን ጨምሮ በሃይማኖት ተቋማት ስር ያሉ ትምህርት ቤቶች የማህበረሰቡን አቅም ያማከለ አገልግሎት እንዲሰጡ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት እንደሚደረገም ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የተቋቋመው የወላይታ ሶዶ አባ ፓስካል ልጃገረዶች ትምህርት ቤት በአሁኑ ወቅት ከቅድመ መደበኛ እስከ 10ኛ ክፍል ባሉ የትምህርት እርከኖች ከ900 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም