ቀጥታ፡

በትግራይና የአማራ ክልሎች የሚገኙ የእግር ኳስ ክለቦች ሲገናኙ በሜዳቸው እንዲጫወቱ ለማድረግ እየተሰራ ነው ተባለ

አዲስ አበባ ጥቅምት 17/2011 በትግራይና የአማራ ክልሎች የሚገኙ እግር ኳስ ክለቦች ለጨዋታ ሲገናኙ በሜዳቸው እንዲጫወቱ ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን  እየተሰራ መሆኑ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ። ፌዴሬሽኑ ከዛሬ ጀምሮ በሚከናወነው የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚሪሊግና በቀጣይ በሚጀመሩ የክለቦች ውድድሮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል። የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት ኮሎኔል አወል አብዱራሂም በዚህ ዓመት ሊጉን በተሻለ  መልኩ ለመምራት ይቻል ዘንድ በርካታ ቅድመ ዝግጅቶች መደረጉን ተናግረዋል። ባለፈው የውድድር ዓመት በተወሰኑ ደጋፊዎች መካከል በተነሳ የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ችግር  ምክንያት በ2010 ዓ.ም ጥር ወር አካባቢ ጀምሮ በአማራና በትግራይ ውስጥ የሚገኙ ክለቦች ሲገናኙ በገለልተኛ ሜዳ እንዲጫወቱ ሲደረገ ቆይቷል። በዚህ ዓመት ግን ይህን ችግር ለመፍታት ከእግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ ከስፖርት ኮሚሽንና ከሁለቱ ክልሎች የተውጣጡ የተለያዩ አመራሮች ጋር  ውይይት እንደተደረገ ጠቁመዋል። ክለቦች በሜዳቸው ጨዋታ ማድረጋቸው ከሁሉ በላይ ክለቦችን ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደሆነ የገለጹት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ጉዳዩን ከስፖርት ኮሚሽን ጋር በአብሮነት እየተሰራ እንደሆነ አብራርተዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ  ''በዚህ ዓመት በእግር ኳስ ሜዳ የሚነሱ የስፖርታዊ ጨዋነት ጉዳይ ለድርድር የማይቀርብና የማንታገሰው ነው'' ብለዋል ኮሎኔል አወል። ባለ ሜዳ የሆኑ ክለቦች ጨዋታው በሰላም እንዲጠናቀቅና የማድረግና እንግዳውን ክለብ በከተማዋ በሰላም ተጫውቶ እስኪወጣ በሀላፊነት ስሜት መጠበቅ እንዳለባቸው ገልጸዋል። ይህ ካልሆነ ግን በእግር ኳስ ክለቦች ጨዋታ ወቅት ጠብ አጫሪ በሆኑ ክለቦች ላይ  ከነጥብ ቅነሳ እስከ ውድድር ማገድ የሚደርስ ቅጣት የሚጣልባቸው መሆኑን ጠቁመዋል። በስፖርታዊ ጨዋነት ለሚያጠናቅቁ  ክለቦች ደግሞ ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ በልዩ ሁኔታ ሽልማት ያገኛሉ ተብሏል። ከዚህ በተጨማሪ ከዚህ በፊት በክለቦች መካከል ቅሬታን ሲፈጥር የቆየው ክለቦች ከሜዳ የሚያገኙትን ገቢ በወቅቱ አለማግኘት ችግር እልባት የሚሰጠው ይሆናል ተብሏል። በተያዘው የ2011 ዓ.ም ክለቦች የሜዳ ገቢያቸውን በተጫወቱ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የሚሰጥበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ተነግሯል። እንዲሁም በዓመቱ መጨረሻ አሸናፊው ክለብ ከዋንጫ ጋር ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ ዳጎስ ያለ የገንዘብ ሽልማት እንዲያገኝ ሁኔታዎች የሚመቻቹ መሆኑን ፌዴሬሽኑ አመልክቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም