የጸጥታ ችግር የሰሊጥ ምርት በወቅቱ እንዳይሰበሰብ ስጋት ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
የጸጥታ ችግር የሰሊጥ ምርት በወቅቱ እንዳይሰበሰብ ስጋት ፈጥሯል
አዲስ አበባ ጥቅምት 17/2011 በኦሮሚያና ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረው የጸጥታ ችግር የሰሊጥ ምርት በወቅቱ እንዳይሰበሰብ ስጋት ፈጥሯል ተባለ። የሰሊጥ ምርት ከደረሰ በኋላ በአጭር ጊዜ ተሰብስቦ ወደ ጎተራ ካልገባ ፍሬው ወደ መሬት በመርገፍ ለብልሽት ይዳረጋል። በግብርና ሚኒስቴር የፕሮሞሽንና ዶክመንቴሽን ቡድን መሪ አቶ ዳንኤል ደንታሞ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ሰሊጥ በሚመረትባቸው የኦሮሚያና ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠረው የጸጥታ ችግር የሰው ኃይል እጥረት በማጋጠሙ ምርቱ በወቅቱ እንዳይሰበሰብ አድርጓል። እንደ አቶ ዳንኤል ገለጻ፣ በአማራና ትግራይ ክልል የሰሊጥ ምርት በተያዘለት የጊዜ ገደብ እየተሰበሰበ ሲሆን በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ አንዳንድ አካባቢዎች ከጸጥታ ጋር በተያያዘ ምርቱን መሰብሰብ አልተቻለም። ሰሊጥ ለአገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከሚያስገኙ ሰብሎች አንዱ ስለሆነ ሁሉም ለጉዳዩ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ አቶ ዳንኤል ተናግረዋል። የቤኒሻኑጉል ጉሙዝ የግብርናና እንስሳት ሃብት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ወዬሳ እንዳሉት፤ በአካባቢ በተፈጠረው አለመረጋጋት በካማሺ ዞን፣ በቡልዲጊሉ ወረዳና በሌሎችም ሰሊጥን በአግባቡ መሰብሰብ አልተቻለም። አርሶ አደሩና ባለሃብቱ ከአካባቢው ነዋሪና ከጸጥታ ሃይሉ ጋር በመተባበር ምርቱን ለመሰብሰበ ጥረት ይደረጋል ብለዋል። በተለይ በአካባቢው ላይ ያለው የጸጥታ ችግር እንዲሻሻል የጉልበት ሰራተኞችም ወደ ማሳው ገብተው እንዲሰበስቡ የመንግስት ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ ባለፈው የምርት ዘመን ከሰሊጥ ምርት 309ሺህ550 ሜትሪከ ቶን ምርት ወደ ወጭ በመላክ 394 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በዘንድሮው ዓመት ከ780 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በሰሊጥ የተሸፈነ ሲሆን ምርቶቹ በአማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ይገኛሉ።