“ትኩረት ይሻሉ”

150
አስማረች አያሌው(ኢዜአ) አካል ጉዳት በሰዎች አእምሮ አልያም አካል ላይ ወይም በሁለቱም በተፈጥሮም ይሁን በሰው ሰራሽ  አደጋ ምክንያት የሚከሰት ነው፡፡ አካል ጉዳተኝነት በአካል ላይ በሚደርስ እክል ከእንቅስቃሴ መወሰንና ከተሳትፎ መገደብን ሊያስከትል ይችላል። የአካል ጉዳት የሰውነት ተግባርና መዋቅር ላይ ችግር ሲያጋጥም የሚከሰት ሲሆን የአካል ጉዳተኛው እንቅስቃሴና ተሳትፎም ባለው ነባራዊ ሁኔታና በአካባቢው ምቹነት ይወሰናል፡፡ ከአለም ጤና ድርጅት ድረገጽ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው አካል ጉዳት የጤና ችግር ሳይሆን አካል ጉዳተኛው ከሚኖርበት አካባቢ ጋር ያለው መስተጋብር የሚገለጽበት ውስብስብ ክስተት በመሆኑ አካል ጉዳተኞች የሚገጥማቸውን ችግር ለመቅረፍ ማህበራዊና አካባቢያዊ እንቅፋቶችን ማስወገድ ይገባል፡፡ አካል ጉዳተኞች ምቹ ሁኔታ ከተፈጠረላቸው እራሳቸውንም ሆነ ሃገራቸውን እንደሚጠቅሙ የአለምም ሆነ የሃገራችን ነባራዊ ሁኔታያሳያል።በአንፃሩ በአመለካከትም ይሁን ከኢኮኖሚ አቅም ውስንነት ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችላቸውን እውቀትና ክህሎት ባለማግኘት ለተለያዩ ማህበራዊ ቀውሶች ሲዳረጉ ይስተዋላል፡፡ አይነስውራን ስለአጋጠሟቸው ችግሮች ምን ይላሉ? አቶ ተመስገን አብዲሳ “ከ10 አመት በፊት በዲፕሎማ በህግ ብመረቅም የትኛውም የመንግስት መስሪያ ቤት የሥራ እድል ሊሰጠኝ ባለመቻሉ የራሴን አነስተኛ የንግድ ስራ ለመስራት ተገድጃለሁ” ይላሉ፡፡ ከሌሎች ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን ያመለከቱባቸው ተቋማት “ለእናንተ ተጨማሪ ጸሃፊ መቅጠር አንችልም”እና  ሌሎች ምክንያቶች እየሰጡ እንደሚመልሷቸው ነው የጠቆሙት፡፡ በኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተማሪ የሆነው  አይነስውሩ ተማሪ ትእግስቱ ዘይዳጋ  እንደ እስኪሪቢቶና ደብተር የሚፅፉባቸው የመማሪያ ቁሶች “ስሌትና ስላይትስ” በየጊዜው ዋጋቸው እየናረ በመሆኑ መፍትሄ ያሻዋል ብሏል፡፡ “ለአካል ጉዳተኛው ቀልፍ ችግር የምለው በተለያየ ምክንያት የሚቆፈሩ መንገዶች እንደነበሩ ሳይመለሱና ጉድጓዶችም ሳይደፈኑ የሚቀሩበት ሁኔታ እኛን ለተጨማሪ የአካል ጉዳት እየዳረገን ነው” ብሏል፡፡ "የቤተመንግስት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት" መምህርት ኩሪ ለገሰ በበኩሏ“እዚህ ደረጃ ለመድረስ አብዛኛውን በራሴ ጥረት በማድረግና በቀሩት የስሜት ህዋሳት ከአእምሮ ጀምሮ በትክክል በመጠቀም ነው “ትላለች፡፡ አሁን ላይ ከማስተማር ሥራ ጎን ለጎን በኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርቷን በኢትዮጵያ ቋንቋና ስነ ፅሁፍ እየተማረች መሆኑንም ገልፃለች፡፡ “ለአይነ ስውራን አንዱ ችግር የመንገድ በየጌዜው መቆፋፈር ነው”ያለችው መምህርቷ የምትኖርበት ሽሮሜዳ ኪዳነምህረት ዋና መንገድ ተቆፋፍሮ ሳይጠናቀቅ ረዥም ጊዜ መቆየቱን ገልፃ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ድንጋይ መቆፋፈርም ደህና መንገድ ፍለጋ ለተጨማሪ መንገድና እንግልት እንደዳረጋትም ጠቁማለች፡፡ “አይነስውራን በልማቱ እየተካተትን መሆኑ ተስፋ ሰጪ ነው” የምትለው መምህርቷ መንግስት ለአይነስውራን ፀሃፊ እንዲቀጠርላቸው፣ ግብአቶችና ማጣቀሻ መጻህፍት እንዲሟሉላቸው በጀት ቢመድብም አንዳንድ ትምህርት ቤቶች እያወቁና ግንዛቤው እያላቸው እንደማይፈፅሙት ትገልፃለች። በመኖሪያ ቤት በኩልም “ለብዙ አከራዮች ሸክም መስለን ስለምንታያቸው ምርጫቸው አይደለንም” በተለይ መሃል ከተማ ለአይነስውራን ለማከራየት ሰዎች ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ከስራ ቦታቸው ለመድረስ ረዥም ትራንስፖርት ለመጠቀም እንደሚገደዱ ነው የጠቀሰችው። አካል ጉዳተኞችስ  ወይዘሪት ውብ አለም መንግስት በፀሃፊነት ሙያ የተሰማራች ሲሆን በፖሊዮ ምክንያት በእግሯ ላይ ጉዳት እንደደረሰባት ትገልፃለች፡፡ “ወላጆቼ ባለብኝ ጉዳት ወደኋላ ሳይሉ ወደ ትምህርት ቤት መላካቸውና ሁልግዜም እንደምችል ስለሚነግሩኝ አሁን ላለሁበት ደረጃ በቅቻለሁ” ትላለች፡፡ አካል ጉዳተኛው የተሟላ እውቀትና ችሎታ እንኳን ቢኖረው ስራ ቀጣሪዎች ቀድመው ጉዳቱን የመመልከት ሁኔታ ይታያል ያለችው ወይዘሪት ውብአለም ተቋማት የሚገኙበት ህንፃም አካል ጉዳተኞች ጉዳያቸውን ለማስፈፀም  የማያስችል መሆኑን ትጠቅሳለች። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የሚሰሩ አንዳንድ አለም አቀፍ ሆቴሎች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ እያደረጉ መሆኑ “መልካም ጅምር ነው” ብላለች፡፡ ህንፃዎች ሲሰሩ የሚያዳልጥ ሴራሚክ መጠቀም፣ የእግረኛ መንገድ በግንባታ ግብአቶችና በድንጋይ እየተዘጉ ማለፊያ ማጣት፣ በተለይ የባቡር ትራንስፖርት አካል ጉዳተኛውን ታሳቢ አድርጎ  አገልግሎት አለመስጠቱ በመንግስትም ሆነ በባለሃብቱ ሊታሰብባቸው የሚገቡ ችግሮች እንደሆኑ ነው የገለፀችው፡፡ “አካል ጉዳተኛው የመስራት ፍላጎት አለው” ያለችው ወይዘሪት ውብአለም ዌልቸር ላይ ቁጭ ብለው አነስተኛ የንግድ ስራ በመስራት ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩ አሉ  ይበልጥ ውጤታማ መሆን እንዲችሉም “ትኩረትና እገዛ ይሻሉ” ብላለች፡፡ መንግሰት የአካል ጉዳተኛ ማህበራትን ከፍ ወደ አለ ተቋም በማሸጋገርና አቅማቸውን በማጠናከር የአካል ጉዳተኞችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ያሉት ደግሞ አቶ አዲስአለም በቀለ ናቸው፡፡ የመንገድ ላይ ንግድ እንዲሁም አንዳንድ ትላልቅ ሆቴሎች፣ ናይትክለቦች፣ ካፌዎችና መጠጥ ቤቶች የእግረኛ መንገድን እንደ ራሳቸው ሃብት በመቁጠር መንገድ ዘግተው መኪና በማቆም አካል ጉዳተኛውን ለተጨማሪ ጉዳት እያጋለጡት መሆኑንም ነው የገለፁት፡፡ እንዲሁም ህብረተሰቡ ባለማስተዋል መንገድ ላይ የሚጥላቸው የውሃ ፕላስቲክ፣ የሙዝ ልጣጭና የሞባይል ካርድ እንዲሁም በመንገድ ላይ የሚጠገኑ መኪኖች የሚያፈሷቸው ዘይቶች  ክራንች ተጠቃሚዎችን የሚያንሸራትቱ በመሆኑ ተገቢ ቦታ እንዲያከማቻቸው ጠቁመው “ባልተገባ ቦታ በሚጣሉት በነዚህ ቁሶች ለተደጋጋሚ መውደቅ ተዳርጌያለሁ” ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ አይነስውራን ብሄራዊ ማህበር ስለተነሱት ችግሮች ምን ይላል? የብሬል መፃፊያ ቁሶች በእርዳታ የሚገቡበት ሁኔታ በመቅረቱና  ከውጪ ሃገራት የሚገዙ በመሆናቸው  ዋጋቸው በመወደዱ ምክንያት ችግሩ መከሰቱን የነገሩን የማህበሩ የትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ ሲሳይ ማሞ  ናቸው። ለአይነስውራን እንደ መፃፊያ የሚያገለግለው “ስሌትና ስላይትስ” አስከ 300 ብር እንደሚሸጥ ጠቁመው ወረቀቱም በተመሳሳይ በሃገር ውስጥ በብዛት ስለማይገኝ በውድ ዋጋ እንደሚገዛ ተናግረዋል፡፡ ማህበሩ ያለትርፍ በገዛበት ዋጋ ለተማሪዎች እንደሚሸጥ የገለፁት አቶ ሲሳይ “ይህ ወጪ ለአብዛኛው የአይነስውራን ተማሪ እንደሚከብድ ይታወቃል” ብለዋል፡፡ ከአለም አቀፍ ለጋሽ ተቋማት ለትምህርት ቤቶች ማሻሻያ መንግስት ከሚያገኘው ፈንድ ለእያንዳንዱ ትምህርት ቤት ከሚመድበው ገንዘብ 4 ከመቶ ልዩ ፍላጎት ላላቸው ተማሪዎች እንዲያውል የሚያስገድድ መመሪያ ቢኖርም አብዛኛው ትምህርት ቤቶች ከግንዛቤ እጦትና ትኩረት ባለመስጠት ምክንያት ተግባር ላይ አለማዋላቸውን ነው የጠቆሙት። ትምህርት ቤቶች የተመደበላቸውን በጀት በግልፅ ማሳወቅ ይገባቸዋል ያሉት አቶ ሲሳይ አይነስውራን ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ችግር ካጋጠማቸው ትምህርት ቤታቸው እንዲያሟላላቸው የመጠየቅና ለዚህም ከማህበሩ የድጋፍ ደበዳቤ ማፃፍ እንደሚችሉም ተናግረዋል፡፡ አይነስውራን የሚፈለገውን ያህል የስራ እድል ተጠቃሚ መሆን ያልቻሉት የሚሰማሩባቸው መስኮች ውስን መሆን ነው ያሉት አቶ ሲሳይ “አይነ ስውራን ማየት ባለመቻላቸው የሚያጡትን ክህሎት የሚያካክስ ስልጠና ያስፈልጋቸዋል፤የሚሰማሩባቸውን መስኮች ለማስፋት ከተለያዩ ተቋማት ጋር የልምድ ልውውጥ እየተደረገ ነው” ብለዋል፡፡ አይነ ስውራንን ታሳቢ ያደረጉ የእግረኛ መንገዶች በከተማ አስተዳደሩ እየተሰሩ መሆኑ አንዱ ለውጥ ቢሆንም በመንገድ ላይ ጉድጓድ ቆፍረው መተው፣ የሚያጋጭ ነገር እና እቃ ማስቀመጥ እንዲሁም ዛፍ መትከል የሚታዩ ክፍተቶች መሆኑን የጠቆሙት የማህበሩ የህዝብ ግንኙነት፣ የቅርንጫፎችና የአባልነት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ገብሬ ተሾመ ናቸው። እንደ አቶ ገብሬ ገለፃ ተቆፍረው የሚተውና ከለላ የሌላቸው ጉድጓዶች እስከ ህይወት መጥፋት አድርሰዋል፣ በጉዳት ምክንያትም ከስራ የተፈናቀሉ ሰዎች አሉ ነው ያሉት። የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ  በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የልዩ ፍላጎት አካቶ ትምህርት ባለሙያ አቶ አስቻለው አድራሮ በዚህ አመት በከተማዋ  የሚገኙ የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች አይነ ስውራን፣  የአካል  ጉዳት ያለባቸውና በድህነት  ምክንያት በልዩ ፍላጎት መታገዝ የሚገባቸው 17 ሺህ ተማሪዎች  መኖራቸውን  ይገልፃሉ። የረዥምና የአጭር ጊዜ ድጋፍ የሚደረግላችው  ተማሪዎች መለየታቸውን የገለፁት አቶ አስቻለው በተለይ ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች በባለሙያ እንዲታገዙ የመምህራን ቅጥር ተከናውኗል። ለአይነስውራን ተማሪዎች የብሬል መፃህፍት እንዲደርሳቸውና በሁሉም ትምህርት ቤቶች ባይሆንም የድጋፍ ሰጪ ማእካላትን በክላስተር በማቋቋም ማጣቀሻ መጽሃፍትንና የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በጋራ እየተጠቀሙ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የብሬል መፅሃፍት በብዛት ስለታተሙ በአሁኑ ሰአት እጥረት እንደሌለ ገልጸው ከስርጭት አኳያ ግን ክፍተት ሊታይ ይችላል ብለዋል፡፡ የአካል ጉዳተኛ መምህራንን ለማገዝ ለአይነስውራን ተጣጣፊ በትር፣ ሌሎች አጋዥ ቁሳቁሶችና መስማት ለተሳናቸው መምህራን ደግሞ መዝገበ ቃላት ለሟሟላት ጨረታ ወጥቶ ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ ግዢ እየተፈፀመ መሆኑን ነው ያወሱት፡፡ ለአይነስውራንና መስማት ለተሳናቸው መምህራን ረዳት ፀሃፊና አስተርጓሚ እንዲቀጠርላቸው ህግና ደንብ እንደሚፈቅድ የገለፁት አቶ አስቻለው  የስራ መደቡና ምን አይነት ባለሙያ የሚለው  ተጠንቶ አለመጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በፊት አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ለአይነስውራን ረዳት ፀሃፊ የሚቀጥሩት ከውስጥ ገቢያቸው “በፈቃደኝነትና በቅንነት”  መምህራኑን ለማገዝ  መሆኑን ነው የገለፁት፡፡ ቢሮው የአይነ ስውራን መምህራንና ተማሪዎች  የማጣቀሻ መፅሃፍትና ሌሎች መረጃዎችን በቀላሉ  ማስጠቀም የሚያስችል ቴክኖሎጂን ከትግራይ ክልል ልምድ እየወሰደ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ የኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች ብሄራዊ ማህበር ስለ ጉዳዩ ምን ይላል? የኢትዮጵያ  የአካል ጉዳተኞች ብሄራዊ ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ማሞ ተሰማ  ማህበሩ የአካል ጉዳተኞችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጥቅም  ለማስከበር እየሰራ መሆኑን ነው የገለፁት፡፡ “አካል ጉዳተኞች ጉዳት እንደሌለባቸው ዜጎች እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማህበሩ የበኩሉን ጥረት ያደርጋል” ያሉት ስራ አስኪያጁ ለአካል ጉዳተኛው፣ ለማህበረሰቡ፣ ለመንግስትና ከሌሎች ባለድርሻዎች  ስለ አካል ጉዳተኝነት እንዲገነዘቡ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ “የአካል ጉዳተኞች ተጠቃሚነት የሚፈለገውን ያህል ያልተረጋገጠው ህጎች፣ መመሪያዎችና አለምአቀፍ ኮንቬንሽኖች ተግባራዊነታቸው የላላ በመሆኑ ነው” ያሉት አቶ ማሞ “ችግሮች አሉ ብለን እጃችንን አጣጥፈን አንቀመጥም ለህጎቹ ተፈፃሚነት ከሁሉም ጋር ተባብረን እየሰራን ነው” ብለዋል፡፡ ማህበሩ ችግሮቹን ለመሻገር አካል ጉዳተኞችን ያማከለ አገልግሎት በተቋማት፣ በትምህርት ቤቶች፣ በጤና ጣቢያዎችና በመዝናኛ ስፍራዎች እንዲኖር ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ አካል ጉዳተኞች የመኖሪያ ቤት፣ የህግ ድጋፍና ስራ ላይ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ማህበሩ ጥረት እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ “አካል ጉዳተኝነት ክስተት ነው” ያሉት አቶ ማሞ በማንኛውም ጊዜና ቦታ እንዲሁም በማንኛውም ሰው ላይ በተፈጥሮም ይሁን  በሰው ሰራሽ ምክንያት ሊከሰት የሚችል በመሆኑ መከላከሉ ላይ የሁሉንም ትኩረትና ርብርብ ይሻል” በማለት ይናገራሉ፡፡ አካል ጉዳተኞች “ህንፃና መንገዶች አካል ጉዳተኛውን ያማከሉ አለም አቀፍ ይዘት ይኑራቸው” የሚለው የሁል ጊዜ ጥያቄያቸው መሆኑንም  ነው አቶ ማሞ   የገለፁት፡፡ የአዲስአበባ መንገዶች ባለስልጣን በየመንገዱ ስለተቆፈሩ ጉድጓዶች የሰጠው ምላሽ በእግረኛ መንገድ ላይ ተቆፍረው በወቅቱ የማይደፈኑ ጉድጓዶችን በተመለከተ ያናገርናቸው  የአዲስ አበባ መንገዶች  ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ጥኡማይ ወልደገብርኤል  በሰጡት ምላሽ የዝናብ ውሃ መቀበያ ቱቦዎች ክዳን በአስፓልት ዳርና በእግረኛ መንገድ ላይ በ50 ሜትርና በ200 ሜትር ልዩነት ይገኛል። እነዚህ ክዳኖች በተለይ አስፓልት ዳር የሚገኙት በከባድ መኪና የመሰበር ሁኔታ ያጋጥማቸዋል፣ አንዳንድ ቦታዎች ላይም መኪኖች እግረኛ መንገድ ላይ ይሄዳሉ፣ ህብረተሰቡም ቆሻሻ ለመድፋት ሲል ክዳኖቹን የሚገነጥልበት ሁኔታ አለ ያሉት አቶ  አቶ ጥኡማይ  በዚህ አመት ክዳናቸው ለተሰበሩና ክፍት ለተተው “ጉድጓዶች” ከ80 ከመቶ በላይ ጥገና ተደርጓል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ የእግረኛ መንገድ እያነጠፉ ያሉት 26 ማህበራት ለስራ ሽሚያ መንገዶችን አስቀድመው በመቆፈርና  በጊዜ ባለመስራት ጉድጓዶችን ክፍት እየተው መሆኑንም ነው ዳይሬክተሩ  የተናገሩት፡፡ አቶ ጥኡማይ ስለ ችግሩ ሲያነሱ “ይህ እንዳይሆን መመሪያ ላይ ተቀምጧል ነገርግን ሲተገበር አይታይም ፤የእኛም የክትትል ማነስ በዚህ በኩል ይታያል” ብለዋል፡፡ ከባለስልጣኑ ፍቃድ ወስደው የመሰረተ ልማት የሚያከናውኑ ተቋማት በጥንቃቄ መጓደል በህብረተሰቡ ላይ ለሚያደርሱት አደጋ በህግ  ተጠያቂ መሆናቸውንም  የገለፁት ዳይሬክተሩ   ከባለስልጣኑ እይታ ውጪ ለሆኑ መሰል ችግሮች ህብረተሰቡ በሚሰጠው ጥቆማ መሰረት ለማስተካከል ዝግጁ መሆናቸውንም  ነው የተናገሩት ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ስለ አካል ጉዳተኞች ምን አሉ? የአካል ጉዳተኞች ስሜትስ? አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ባስቀመጡት የትኩረት አቅጣጫ “የአካል ጉዳተኛ እህቶቻችንና ወንድሞቻችን ጉዳይ በምንሄድበት የለውጥ ጎዳና አፅንኦት የሚሰጠው ጉዳይ ነው። በሃገራችን በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ ምክንያት የአካል ጉዳት ቢያጋጥማቸውም እንደ ቁጥራቸውም ሁሉ አስተዋፅኦዋቸውም የላቀ ነው፤ ተገቢውን ትኩረትም ይሻሉ፡፡ አካል ጉዳተኝነት አለመቻል አለመሆኑን ከማሳየት ባሻገር የምጡቅ አእምሮ ባለቤት መሆናቸውን ያስመሰከሩ በርካታ ዜጎች መኖራቸውንና አቅማቸውን በሙሉ በአገር ግንባታ ጥረት ውስጥ አሟጠን ካልተጠቀምን ጥረታችን ሙሉ ሃገራዊ ምስል አይኖረውም። አካል ጉዳተኞችን በማንኛውም ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በማሳተፍ ተጠቃሚነታቸውን ለማጎልበት አበክረን እንሰራለን” ጠቅላይ ሚኒስተሩ “አካል ጉዳተኞች በፖለቲካው፣በኢኮኖሚና በማህበራዊ ጉዳዮች በተሟላ ሁኔታ እንዲሳተፉ ትኩረት ይደረጋል” ባሉት ንግግርም ተስፋ ማድጋቸውን ነው አካል ጉዳተኞች የገለፁት፡፡ “አካል ጉዳተኛው አጋዥ ካገኘ የመስራት ፍላጎት አለው” ያሉት  አቶ ተመስገን አዲሱ አመራር የሀገሪቱን አንድነት በማጠናከር ሁሉንም ዜጋ ያማከለ ለውጥ ያመጣል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ ሁላችንም አንድ ሆነንና ተባብረን  ከሰራን የሚያቅተን ነገር የለም ያለው ተማሪ ትእግስቱ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ወደፊት በፖለቲካው፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚው ዘርፍ አካል ጉዳተኛውን ተጠቃሚ ያደርጋሉ ብሎ እንደሚያምን ግልጿል፡፡ “አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አካል ጉዳተኞች መስራት እንደሚችሉ መናገራቸው ለእኛ ትልቅ ኃላፊነት ነው፣ ወደ ተግባር ለመግባትም ያነሳሳናል”ያለችው ደግሞ ወይዘሪት ውብ አለም ናት። በጥቅሉ ሲታይ በአለማችን 1 ቢሊየን በሃገራችን ደግሞ 15 ሚሊየን የአካል ጉዳተኞች እንዳሉ መረጃዎች የሚጠቁሙ ሲሆን የሃገር እድገት የተሟላ እንዲሆን አካል ጉዳተኞችን በሁሉም ዘርፍ ማሳተፍና ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ ነው እንላለን፡፡  ቸር እንሰንብት!!                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም