ቀጥታ፡

የሳንሱሲ -ታጠቅ ኬላ መንገድ ፕሮጀክት ከተጀመረ አንድ አመት ቢያስቆጥርም እየተጓተተ ነው

አዲስ አበባ 16/2011 የሳንሱሲ - ታጠቅ ኬላ 14 ኪሎ ሜትር መንገድ ፕሮጀክት ከተጀመረ አንድ ዓመት እያስቆጠረ ቢሆንም ከአፈር ጠረጋና ድልዳሎ ያለፈ መሄድ አልቻለም። ህዳር 2010 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው ይህ የመንገድ ግንባታ በአስፋልት ኮንክሪት የሚገነባ ነው። በሶስት ዓመት ይጠናቀቃል ቢባልም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ 14 በመቶ መጠናቀቅ ሲገባው ግንባታው 6 በመቶ ብቻ ደርሷል። የመንገዱን ግንበታ የሚያስኬደው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዛሬ የግንባታውን ደረጃ ለመገናኛ ብዙሃን ሲያስጎበኝ እንደተመለከትነው አብዛኛው የመንገዱ ግንባታ እንቅስቃሴ የተቀዛቀዘ ነው። ለግንባታው መጓተት ከወሰን ማስከበር ጋር የተያያዙ የቤቶችና ንብረቶች ወቅቱን ጠብቆ አለመነሳት የመንገዶች ባለስልጣን በምክንያትነት ያቀርባል። የባለስልጣኑ የህዝብ ግንኙነት ዳሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ እደተናገሩት ችግሩን ለመፍታት ከሚመለከታቸው ጋር ውይይቶች ቢደረጉም በተግባር እየተፈጸመ አይደለም። የአካባቢው ነዋሪዎች በበኩላቸው የካሳና ምትክ ቦታ ይሰጣችኋል ቢባሉም እስካሁን መፍትሄ አለማግኘታቸውን ይናገራሉ። የአካባቢውአቶ ሙኬ በቀለ የቀበሌ ቤት ስለሆነ ካሳ አይከፈልም አሉን የት እንውደቅሲሉ ተናግረዋል፡፡ ወይዘሮ ትግስት ተካ በበኩላቸው የግምት ብር ወስጃለሁ መሬት ግን እየጠበክሁ ነው መሬት ይሰጣችኋል ግምታችሁን ውሰዱ ብለውን እስካሁን መሬት ሊሰጡን አልቻሉም በማለት ይናገራሉ፡፡ ከ176 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በኢትዮጵያ መንግስት የሚገነባው ይህ የመንገድ ፕሮጀክት ችግሮቹ ተፈተው ግንባታው ካልተፋጠነ ወጪው ሊጨምር ይችላል የሚል ስጋትም ፈጥሯል። የመንገዱን ግንባታ ለማከናወን ኮንትራቱን የወሰደው አሰር ኮንስትራክሽን የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ያሬድ ቢያድግልኝ እንደሚናገሩት ሙሉ ለሙሉ ቤቶችና ንብረቶች ሳይነሱ መስራት አክሳሪ ከመሆኑ ባለፈ ለጥራትም አይመከርም። የቡራዩ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ጫሊ ቤኛ በበኩላቸው የአማካሪ ድርጅት በወቅቱ አለመመደብና የካሳ ክፍያ ገማች ኮሚቴ በወቅቱ አለመቋቋም ቤቶችን በፍጥነት እንዳይነሱ ካደረጉ ጉዳዮች መካከል ይጠቅሳሉ ብለዋል። አሁን ችግሩን ለመፍታትና ግንባታውን ለማፋጠን ከኢትዮጵያ መንገዶችና ግንባታውን ከሚያከናውነው ስራ ተቋራጭ ጋር እየሰሩ መሆኑንም ነው የሚናገሩት። የካሳ አከፋፈልንና ምትክ ቦታን በተመለከተ ህጋዊ ይዞታ ያላቸው 92 ነዋሪዎች ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ ካሳ የወሰዱ ሲሆን 72 ነዋሪዎች ደግሞ በሂደት ላይ መሆናቸውንም አንስተዋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ቅሬታ ያለው ነዋሪ ቅሬታውን ህጋዊ በሆነ መንገድ ማቅረብ እንደሚችል ገልጸው እስካሁን ግን የቀረበ ቅሬታ አለመኖሩን ተናግረዋል። የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አካል የሆነው ይህ የመንገድ ፕሮጀክት በአንድ ጊዜ ግራና ቀኝ አሁን እያሳለፈ ካለው ሁለት መኪና አራት ለማሳለፍ የታሰበ ነው። መንገዱ ሲጠናቀቅም የአካባቢው ማህበረሰብ በእለት ተእለት እንቅስቃሴው የትራንስፖርት አገልግሎትን ከማሳለጥ ባለፈ የኢኮኖሚ ፋይዳውም የጎላ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም