ቀጥታ፡

''የጤናውን ዘርፍ ልማት ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የጤና ባለሙያዎችና አጋር ድርጅቶች መሥራት ይገባቸዋል''_ሚኒስትር ዶክተር አሚር

መቀሌ ጥቅምት 16/2011 የጤናውን ዘርፍ ልማት ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የጤና ባለሙያዎችና አጋር ድርጅቶች መሥራት እንደሚገባቸው የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን አሳሰቡ። የክልሎች ጤና ቢሮዎች በ2011 በጀት ዓመት የሚያከናውኗቸው ዝርዝር ሥራዎች ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር ስምምነት ተፈራርመዋል። ሚኒስትሩ በመቀሌ ከተማ የተካሄደው 20ኛው ዓመታዊ የጤና ዘርፍ ልማት ጉባዔ መዝጊያ ላይ እንዳሉት በዘርፉ የሚከናወኑ ሥራዎችን   ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳዳግ  በየደረጃው የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች በትጋትና ኃላፊነት ስሜት መንቀሳቀስ አለባቸው። በዘርፉ የሚንቀሳቀሱ አጋር ድርጅቶችም የሚያደርጉትን እገዛ ማጠናከር ይጠበቅባዋል ብለዋል። በዘርፉ የሚታየውን የአሰራር መንዛዛት በማስቀረት ጥራት ያለውና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚሰሩ በጉባዔው የተሳተፉ የጤና ባለሙያዎች ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል። ባለሙያዎቹ ወደየመጡባቸው አካባቢዎች ሲመለሱ በዘርፉ የሚታዩትን ችግሮች ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ አመልክተዋል። ከጤና ባለሙያዎች መካከል የግል የጤና ተቋማትን ወክለው የተገኙት አቶ ሁሴን ኑሩ መንግሥት በዘርፉ የሚሰሩ የግል ተቋማትን እንቅስቃሴ አበረታች መሆኑን ገልጸው፣ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ የተያዙ ግቦችን ለማሳካት ተቀናጅተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ስኳር ህሙማን ማህበር የፕሮግራም ማናጀር አቶ አብዱከሪም ሙሳ በበኩላቸው፣ ለኅብረተሰቡ ተደራሽ የሆነ የጤና አገልግሎት ጥራት ባለው መልኩ ለማቅረብ ባለሙያዎችና አጋር ድርጅቶች ከሚኒስቴሩ ጋር ተቀናጅቶ መሥራት ወሳኝ መሆኑን ይገልጻሉ። የወረዳ የጤና ትራንስፎርሜሽን በማረጋገጥ ጥራት ያለውና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ተቀናጅተው ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል። ዕቅዱን የሚሳካው ሚኒስቴሩ በሚያደርገው ጥረት ብቻ ሳይሆን፤ አጋር አካላት ድርሻቸው ሲያበረክቱ መሆኑን የተናገሩት አቶ አብዱልከሪም፣ ማህበራቸው ይህን ለማገዝ 30 ሺህ አዋቂዎችና ሰባት ሺህ ህጻናት የስኳር ህሙማንን በመርዳት ላይ መሆኑን በአብነትነት አቅርበዋል። የሶማሌ ክልል የጤና ኤክስቴሽን ባለሙያ ወጣት ይሩ መሐመድ ዓወድ በበኩሏ፣ጉባዔው  በክልሉ ያለውን የጤና ተደራሽነት ችግር ለመፍታትና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት የምትሰራበት ተሞክሮ እንዳገኘችበት ትናገራለች። በክልሉ ባደረጉት የመስክ ምልከታም በጤናው ዘርፍ ልማት የሴቶችን ተሳትፎ ለመገንዘብ አስችሎኛል ብላለች።በዚህም በክልሉ ያየችውን መልካም ተሞክሮ በክልሏ ለማስፋት እንደምትሰራ ገልጻለች። የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከዘጠኙ ክልሎችና ከሁለቱ ከተሞች አስተዳደሮች ጤና ቢሮዎች በያዝነው በጀት ዓመት የሚያከናውኗቸው ዝርዝር ሥራዎች ጋር የሚሰራበትን ስምምነት በዚሁ ወቅት ተፈራርሟል። ለሦስት ቀናት በተካሄድ ጉባዔ በጤናው ዘርፍ የሚንቀሳቀሱ ከአንድ ሺህ በላይ ባለድርሻዎች ተሳትፈዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም