ቀጥታ፡

በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር የሰራተኞች ማህበራት መጠናከር ወሳኝ ሚና እንዳለው ተገለፀ

አዲስ አበባ ጥቅምት 16/2011 በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር የሰራተኞች ማህበራት መጠናከር ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ተገለፀ። የአፍሪካ ቀንድ የሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን የምስረታ ጉባኤ በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ተጀምሯል። በጉባኤው የመወያያ ሐሳብ ያቀረቡት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጎረቤት አገሮችና የኢጋድ ጉዳዮች ሓላፊ አምበሳደር መሐመድ ድሪር እንደገለፁት በአፍሪካ ቀንድ የሚታየውን የሰላምና መረጋጋት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሰራተኛ ማህበራት ሚና ወሳኝ ነው። በአፍሪካ ቀንድ የሚገኙ ሰራተኞች ህይወት በሚፈጠሩ አለመረጋጋቶችና ግጭቶች ተጋላጭና የበርካታ ችግሮች ገፈት ቀማሽ ናቸው ብለዋል። ይሄ ችግር የሚፈታው በሰላም ማስከበርና በፀጥታ ኃይል ብቻ አይደለም፤ የግሉ ዘርፍ በተለይ የሰራተኛ ማህበራት ራሳቸውን አጠናክረው በያሉበት መስክ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባልም ነው ያሉት። የኢትዮጵያ መንግስት እንዲሁም በአጠቃላይ የኢጋድ አገሮች በአንድ ተግባብተን ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር እየሰራን ነው ብሏል አምባሳደሩ። በዓለም አቀፍ የሰራተኞች ድርጅት የሰራተኞች ስፔሻሊስት ካቡ ምባን በጉባኤው የሰራተኛ ማህበራት የሰላምና መረጋጋትን በመፍጠር ረገድ ያላቸውን ሚና የሚያሳይ ጥናታዊ ፅሑፍ አቅርበዋል። የሰራተኛ ማህበራት መጠናከር በሁሉም የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች ያላቸውን የራሳቸውን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባሻገር ወደ ግጭትና አለመረጋጋት ሊመሩ የሚችሉ ችግሮችን በእንጭጩ ለመፍታትም አጋዥ ናቸው ብለዋል። በአፍሪካ ቀንድ ባሉ ሰራተኞችና በአጠቃላይ ህዝቡን የሚያጋጥሙ ችግሮች ተመሳሳይ በመሆናቸው በጋራ ለመፍታት አንድ ጠንካራ የአፍሪካ ቀንድ የሰራተኞች ማህበር መኖር አስፈላጊ መሆኑንም እንዲሁ። ከዚህ በተጨማሪ በአፍሪካ ቀንድ አገሮች የሚስተዋሉ የፖሊሲ ችግሮችና የአድልዎና ምቹ ያልሆኑ የሥራ ቦታዎችን ለማስወገድ የሚደረገውን ጠንካራ ትግል ለማድረግ የማህበራት መጠናከር አስፈላጊ መሆኑንም አስረድተዋል። በነገው ዕለት ምስረታው ይፋ የሚደረገው የአፍሪካ ቀንድ የሰራተኞች ኮንፌዴሬሽንም የሰራተኞች ችግርችን በመፍታት ለአካባቢው ሰላምና መረጋጋት የራሱን አስተዋፅኦ የማድረግ ሰፊ ዕድል እንዳለው ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት  ኮንፌዴሬሽን ፕረዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ በበኩላቸው የአፍሪካ ቀንድ የሰራተኞች ማህበራት በጋራ ተቀራርበው መስራት የአካባቢውን ሰለም ለማስጠበቅና ችግሮች ወደ ግጭት ደረጃ ሳያድጉ ለመፍታት ይረዳል ብለዋል። የምስራቅ አፍሪካ ወጣቶች በአካባቢው በሚስተዋለው የሰላምና መረጋጋት ችግርና የተሻለ ሥራ ፍለጋ ምክንያት መካከለኛው ምስራቅን ጨምሮ ወደ ተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች እንደሚሰደዱም ገልፀዋል። በትውልድ አገራቸውና ተሰደው በሚሄዱበት አካባቢ የሚያጋጥሙዋቸውን ችግሮች ለመፍታትም የአፍሪካ ቀንድ ማህበራት በአንድ ሰብሰብ ብለን ከሰራን ጠንካራና የሚደመጥ ድምፅ መፍጠር እንችላለን ሲሉም ተናግረዋል። በጉባኤው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምበሳደር ምስጋናው አረጋ እንደገለፁት የሰራተኛ ማህበራት ተጠናክረው በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ላይ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል። የተደራጁና የተጠናከሩ ማህበራት ከተፈጠሩ በአፍሪካ ቀንድ ሰላም ለማስጠበቅና የተሻሉ የልምድ ልውውጦች ለማድረግ ዕድል አላቸው ሲሉም ተናግረዋል። በአፍሪካ ቀንድ የሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ምስረታ ከኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ጁብቲ፣ ሶማሊያና ኡጋንዳ የተወጣጡ የሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽኖች ተወካዮች በምስረታ ጉባኤው እየተሳተፉ ይገኛሉ። ጉባኤው በነገው ዕለት የኮንፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ በማፅደቅ፣ የቦርድ አባላትና አመራሮች በመምረጥ ምስረታውን ይፋ እንደሚደረግ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም