በታንዛኒያ ሕይወታቸው ያለፈ ኢትዮጵያዊያን አስከሬን ወደ አገር ቤት ሊመጣ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በታንዛኒያ ሕይወታቸው ያለፈ ኢትዮጵያዊያን አስከሬን ወደ አገር ቤት ሊመጣ ነው
አዲስ አበባ ጥቅምት 16/2011 ከኬንያ ሞምባሳ ወደብ ተነስተው ወደ ታንዛኒያ በጀልባ በመጓዝ ላይ እያሉ በደረሰ የመስጠም አደጋ ህይወታቸውን ያጡ ስምንት ኢትዮጵያዊያን አስከሬን ወደ አገር ቤት ሊመለስ ነው። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢዜአ እንዳስታወቀው በአደጋው ሕይወታቸው ያለፈና የተረፉ ዜጎችን ጉዳይ በተመለከተ ከታንዛኒያ መንግስት የሥራ ኃላፊዎች እየተሰራ ነው። ጥቅምት 12 ቀን 2011 ዓ.ም ከኬንያ የወደብ ከተማ ሞምባሳ 13 ኢትዮጵያዊያንን አሳፍራ በታንዛኒያ የባህር ዳርቻ ታንጋ ግዛት የደረሰችው ጀልባ በማዕበል ተመታ ስምንት ኢትዮጵያዊያን በመስመጥ አደጋ ሕይወታቸው ሲያልፍ አምስቱ መትረፋቸው ይታወሳል። በታንዛኒያ ዳሬሰላም የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በአደጋው ሕይወታቸው ያለፈና የተረፉ ዜጎችን ጉዳይ በተመለከተ ከአገሪቱ መንግስት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ወደ አገራቸው በሚመለሱበት ጉዳይ ላይ እየሰራ ይገኛል። ሚኒስቴሩ በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎች የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን በመግለጽ ዜጎች እንዲህ ዓይነት አደገኛ ጉዞ ከማድረግ እንዲቆጠቡ መልዕክት ማስተላለፉን ሚኒስቴሩ በላከው መግለጫ አስታውቋል።