ቀጥታ፡

የደቡብ ኮርያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ለመሰማራት ፍላጎት አላቸው

አዲስ አበባ ጥቅምት 16/2011 የደቡብ ኮሪያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ተገለጸ። በቅርቡ በሴኡል ከተማ በተካሄደው የኢትዮጵያ ቢዝነስ ማስተዋወቂያ መድረክ ላይ ግዙፍ የኮርያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ለመሰማራት ጥያቄ ማቅረባቸውን ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መረጃ ያመላከተው። በደቡብ ኮሪያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሚሲዮን መሪ በአቶ ቤኩማ መርዳሳ የተመራ ልዑካን ቡድን ጥቅምት 14 ቀን 2011 ዓ.ም ወደ ቡሳን ከተማ በማቅናት በኢትዮጵያ በተለያዩ ኢንቨስትመንት መስኮች ለመሰማራት ፍላጎት ያሳዩ ኩባንያዎችን አነጋግሯል። በተካሄደው ውይይትም ዴሃን ስቲል የተባለ ኩባንያ በአንድ ሚሊዮን ዶላር ካፒታል በብረታ ብረት ምርት ግብዓት ቁፋሮና ማምረቻ ዘርፍ በኢትዮጵያ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳለው አስታውቋል። ቪዥን ቴክ የተባለ ኩባንያ ደግሞ ዝቅተኛ ካርቦን ልቀት ያላቸውና ኃይል ቆጣቢ የኤሌክትሪክ ውጤቶችና በአምፖል ምርት ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳለው ሚኒስቴሩ ገልጿል። እንዲሁም ከስድስት መቶ ሚሊዮን ዶላር በላይ ካፒታል የሚያንቀሳቅሰውና ስሙ ያልተጠቀሰ ሌላ ኩባንያም በተመሳሳይ ፍላጎት ካሳዩት ኩባንያዎች መካከል እንደሚገኝ ተጠቅሷል። በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው የደቡብ ኮርያ የቢዝነስ ልዑካን ቡድን በአገሪቱ ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጭ ለማየትና ከመንግስት ጋር ውይይት ለማድረግ በመጪው ታህሳስ 2011 ዓ.ም አጋማሽ ላይ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ዝግጅት እያደረጉ መሆኑንም መረጃው ጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም