ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የተሰጣቸውን ሃላፊነት በብቃት የሚወጡ ናቸው-የቀድሞ የኢፌድሪ ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ - ኢዜአ አማርኛ
ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የተሰጣቸውን ሃላፊነት በብቃት የሚወጡ ናቸው-የቀድሞ የኢፌድሪ ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ
አዲስ አበnባ ጥቅምት 16/2011 ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የተሰጣቸውን ሃላፊነት በብቃት የሚወጡ ናቸው ሲሉ የቀድሞ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት አቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስ ተናገሩ፡፡ ለበርካታ ዓመታት በአገር፣ በአህጉራዊና አለም አቀፋዊ ተቋማት በከፍተኛ የስራ ኃላፊነት ያገለገሉት ሳህለወርቅ ዘውዴ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንትነቱን ኃላፊነት ከዶክተር ሙላቱ ተሾመ ትናንት ተረክበዋል፡፡ ይህንን ተከትሎ የተለያዩ የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክቶች እየቀረቡላቸው ነው፡፡ ለስራ ያላቸውንም ብቃት እየመሰከሩ ነው፡፡ የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ፤ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን በቅርብ እንደሚያውቋቸው ተናግረው የተሰጣቸውን ሃገራዊ ኃላፊነት በብቃት የሚወጡ መሆናቸውንም መስክረዋል፡፡ "ሴቶች በየትኛውም ዓይነት የሥልጣን እርከን ላይ ቢቀመጡ ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎች ለመስራት ትልቅ ዓቅም አላቸው" ያሉት የቀድሞ የኢፌድሪ ፕሬዝዳንት ግርማ "ሴቶች ከወንዶች በተሻለ ቆራጥና ታማኝ ናቸው" ሲሉም ገልጸዋቸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ "በቅርቡ በሀገሪቱ እየታየ ያለው ለውጥ እጅግ አስገራሚ ነው" የሚሉት አቶ ግርማ፤ በታሪክ ታይቶ የማይታወቀውን የሴቶች ሃምሳ በመቶ የካቢኔ ምርጫንም አድንቀዋል፡፡ "ፕሬዝዳንት ማለት አገልጋይ ማለት ነው" የሚሉት አቶ ግርማ "የትኛውም ፕሬዝዳንት ህዝቡን ማገልገል አለበት፤ ህዝቡ ችግሩ ምንድነው? ብሎ ቀርቦ የሚጠይቅ ፕሬዝዳንት መሆን አለበት፤ ምክንያቱም ዞሮ ዞሮ ዋና አላመው የሕዝቡን ኑሮ መቀየር እና ኢትዮጵያን ከፍ ማድረግ ነው" ብለዋል፡፡ ይህን ኃላፊነት ደግሞ አዲስ የተመረጡት አምባሳደር ሳህለወርቅ "የብዙ ዓመት ልምዳቸውን ተጠቅመው በአግባቡ እንደሚወጡት እምነቴ ነው" ብለዋል፡፡ የቀድሞ የኢፌድሪ ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ በወቅቱ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት የነበሩት ነጋሶ ጊዳዳ ከስልጣን መልቀቅን ተከትሎ ወደ ስልጣን የመጡ ሲሆን ለ12 ዓመታትም በፕሬዝዳንትነት ማገልገላቸው ይታወሳል፡፡