ዓመታዊው የወርልድ ቴኳንዶ የግል የበላይነት ሻምፒዮና ዛሬ ተጀምሯል - ኢዜአ አማርኛ
ዓመታዊው የወርልድ ቴኳንዶ የግል የበላይነት ሻምፒዮና ዛሬ ተጀምሯል
አዲስ አበባ ጥቅምት 16/2011 ዓመታዊው የወርልድ ቴኳንዶ የግል የበላይነት ሻምፒዮና ዛሬ በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ተጀምሯል። ለሁሉም ክፍት በሆነው ሻምፒዮናው በወንዶች ከ 52 እስከ 80 ኪሎ ግራም በሴቶች ከ46 እስከ 67 ኪሎ ግራም በአጠቃላይ በ12 ኪሎ ዓይነት 115 ተወዳዳሪዎች ይሳተፋሉ። የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ዳዊት አስፋው ለኢዜአ እንደገለጹት የሻምፒዮኑ ዓላማ በወርልድ ቴኳንዶ ብቁና ጠንካራ ተወዳዳሪ በማፍራት ኢትዮጵያን በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያስጠሩ ስፖርተኞችን መመልመል ነው። ሻምዮናው የውድድር አማራጮችን በመፍጠር ታዳጊ ወጣት ስፖርተኞች እንዲሳተፉ ከማድረግ አንጻር የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ተናግረዋል። በተጨማሪም በሞሮኮ በጥቅምት ወር 2012 ዓ.ም በሚካሄደው የመላው አፍሪካ ውድድር ብቁ ስፖርተኞች ከውድድሩ እንደሚመለምሉም ጠቅሰዋል። በጥር 2011 ዓ.ም ተመሳሳይ ውድድር ለማዘጋጀት እቅድ መያዙን ገልጸው ስፖንሰሮች ከተገኙ ተጨማሪ ሶስተኛ ውድድር የማዘጋጀት ፍላጎት እንዳለም አቶ ዳዊት አስረድተዋል። በተያዘው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ የወርልድ ቴኳንዶ ክለቦች ውድድር ለመጀመር የሚያስችል ጥናት መካሄዱንና በሰኔ 2011 ዓ.ም ውድድሩን ለማካሄድ እቅድ መያዙንም አመልክተዋል። በተጨማሪም ዓመታዊው የኢትዮጵያ የወርልድ ቴኳንዶ ሻምፒዮና እንደሚካሄድና ውድድሮች መብዛታቸው ስፖርቱን ለማስተዋወቅና ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ይረዳል ብለዋል። ከዚህ በፊት ከተካሄዱ የግል የበላይነት ውድድሮች ኢትዮጵያን በአፍሪካ ደረጃ ያስጠሩ ስፖርተኞች ተገኝተዋል ያሉት ፕሬዚዳንቱ ሰለሞን ቱፋና ታሪኩ ግርማ ባለፈው ዓመት በሞሮኮና በአልጄሪያ በተካሄዱ ውድድሮች ያስገኙትን የወርቅ ሜዳሊያ በማሳያነት ጠቅሰዋል። በሻምፒዮናው የመጀመሪያ ቀን መርሃ ግብር በወንዶች በ58 ኪሎ ግራም በሴቶች በ46 ኪሎ ግራም ጨዋታዎች ይደረጋሉ። በአጠቃላይ የውድድሩ አሸናፊዎች ከሜዳሊያ ሽልማት በተጨማሪ በሁሉም የክብደት ዘርፍ ከአንድ እስከ ሶስት ለሚወጡ ተወዳዳሪዎች በቅደም ተከትል የ10፣ 5 እና 3 ሺህ ብር ሽልማት እንደሚበረከትላቸው ተገልጿል። በሁለቱም ጾታ ምርጥ ስፖርተኛ ተብለው ለሚመረጡ ተወዳዳሪዎች የ5 ሺህ ብር ሽልማት እንደሚሰጥና አዲስ ለሚታዩ ወጣት ተፋላሚዎች የ5 ሺህ ብር የማበረታቻ ሽልማት ይሰጣል። በተያዘው ዓመት መሰል ውድድሮች የሚካሄዱ ሲሆን በየውድድሩ የተሳትፎ ነጥብ በመመዝገብ በዓመቱ መጨረሻ ለአጠቃላይ አሸናፊዎች ከፍተኛ ሽልማት እንደሚበረከትም በሻምፒዮናው መክፈቻ ወቅት ተገልጿል። ዓመታዊው የወርልድ ቴኳንዶ የግል የበላይነት ሻምፒዮና እስከ ጥቅምት 19 ቀን 2011 ዓ.ም ይቆያል። የኮሪያውያን የባህል ስፖርት በሚል የሚታወቀው ወርልድ ቴኳንዶ ከሰውነት ፍልሚያ ባሻገር ብዙ ጥበባዊ ይዘቶችን (ስልቶችን) በውስጡ ያካተተ ስፖርታዊ ክንዋኔ ነው። አዕምሮንና ሰውነትን ማሰልጠን ጨምሮ ህይወትን በአግባቡ ለመምራት የሚያግዝ የስፖርት ዓይነት እንደሆነም በዘርፉ ያሉ ምሁራን ይናገራሉ። የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን በ1995 ዓ.ም በብሔራዊ ደረጃ የተቋቋመ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ስፖርቱ ከአትሌቲክስ በመቀጠል በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በአህጉር ደረጃ ውጤት በማምጣት የኢትዮጵያን ስም በማስጠራት ላይ ይገኛል።