ቀጥታ፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ አፍሪካ ህብረትና ኢጋድ ለፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ የደስታ መግለጫ አስተላለፉ

አዲስ አበባ ጥቅምት 16/2011 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ መሃመትና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ዋና ፀሃፊ ማህቡብ ማዐሊም ለፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የደስታ መግለጫ አስተላለፉ። የሶስቱ ተቋማት መሪዎች የፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ መመረጥ ሴቶች በፖለቲካው መስክ ያላቸውን ስኬት አጉልቶ የሚያሳይ መሆኑን ገልፀዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በፕሬዝዳንቷ ሹመት የተሰማቸውን ደስታ በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል። ዋና ፀሐፊው የፕሬዝዳንቷ ሹመት የሴቶች አመራርነት ለሰላም ቁልፉ መንገድ እንደሆነ ለአፍሪካ ማሳያ እርምጃ አድርገው እንደሚቆጥሩት ተናግረዋል። የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ መሃመት በበኩላቸው፤ በአገሪቷ ሴት ርዕሰ ብሄር ሆና ስትሾም የኢትዮጵያ ሴቶችን ወደ አመራርነት በማብቃት ሂደትና በስኬታማ የፖለቲካ ውሳኔ ሰጪነት እንዲመጡ እየተደረገ ያለው ጥረት አርአያ መሆኑን ገልፀዋል። አገሪቱ በቅርቡ ሴቶችን በካቢኔ ምስረታ ግማሽ በግማሽ በማድረግ  ማዋቀሯን አውስተው በተለይም የሴት ፕሬዚዳንት ምርጫ አገሪቱ ሴቶችን ከማብቃት አኳያ ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገሯንና ይህም ለአፍሪካ ጭምር ኩራት መሆኑን ገልፀዋል። የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አስተዳደር እየወሰደ ያለውን የለውጥ እርምጃዎች ያደነቁት ኮሚሽነሩ ለፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴም የእንኳን ደስ ያልዎት መልእክትና በቀጣይ ስራቸውም ስኬትን ተመኝተዋል። የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ዋና ፀሃፊ ማህቡብ ማዐሊም በበኩላቸው ኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝዳንት በመምረጧ በከፍተኛ የመንግስት አመራር ላይ እንዲወጡ ትልቅ ታሪክ ሰርታለች ሲሉ ዋና ፀሀፊው ገልፀዋል። ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በመመረጣቸው የኢትዮጵያን ህዝብና መንግስት አንኳን ደስ አላችሁም ብለዋል። ኢጋድ ከአዲሷ ተመራጭ ፕሬዚዳንት ጋር በጋራ ለመስራት ያለውን ዝግጁነትም ገልፀዋል ዋና ፀሃፊው ማህቡብ ማዐሊም። በተመሳሳይ መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገው የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ዋና ፀሐፊ ዶክተር ቬራ ሶንግዌ የረጅም ዓመታት የዲፕሎማሲ ልምድ ባለቤት የሆኑት ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በታታሪነት ባገኙት ከፍተኛ ኃላፊነት የተሰማቸውን ደስታና የእንኳን ደስ አሎት መልክት በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል። መቀመጫውን ብራሰልስ ያደረገው የአውሮፓ ህብረት በበኩሉ የፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ መመረጥ  በኢትዮጵያ ሴቶች በፖለቲካው መስክ ያላቸውን ስኬት አጉልቶ የሚያሳይ መሆኑን በመጥቀስ ከፕሬዚዳንቷ ጋር በቀጣይ በጋራ እንደሚሰራና ለኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት የደስታ መግለጫ አስተላልፈዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም