አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከኤርትራ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከኤርትራ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ ጥቅምት 16/2011 በኤርትራ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከኤርትራ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ማጠናከር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ውይይት አካሂደዋል። አምባሳደር ሬድዋን ከኤርትራ የትምህርት፣ የግብርና፣ ትራንስፖርትና የኮሙኒኬሽን እንዲሁም የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሮች ጨምሮ የማዕከላዊ አስተዳደር ገዥ ጋር ተገናኝተው የሁለቱን አገራት ግንኙነት የበለጠ ማሳደግ በሚቻልበት ጉዳዮች ላይ ውይይት ማካሄዳቸውን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ገልጿል። አምባሳደሩ በዚህ መሰረት ከኤርትራው የትምህርት ሚኒስትር ሰመረ ርዕሶም፣ የግብርና ሚኒስትሩ አረፍአይኔ ብርሃኔ ፣ የትራንስፖርትና ኮሙኒኬሽን ሚኒስትሩ ተስፋስላሴ ብርሃኔ፣ የንግድና ኢንዱስትር ሚኒስትር ነስረዲን በኬት እና የማዕከላዊ አስተዳደር ገዥ ከሆኑት ሜጀር ጄኔራል ሮመዳን ኦስማን ጋር ነው የተወያዩት። ኢትዮጵያ በትምህርት፣ በግብርና፣ በትራንስፖርት፣ በኮሙኒኬሽን እንዲሁም በንግድና ኢንዱስትሪ መስኮች ከኤርትራ ጋር በትብብር የመስራት ፍላጎት እንዳላትም አምባሳደር ሬድዋን በዚሁ ጊዜ ገልፀዋል። ይህም የሁለቱ እህትማማች ህዝቦችን የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የገለፁት አምባሳደሩ ሁለቱ ህዝቦችን የበለጠ የሚያቀራርቡና ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሁለትዮሽ ግንኙነቶች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸውም ብለዋል። የኤርትራ መንግስት የሥራ ኃላፊዎች በበኩላቸው የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ እንቅስቃሴዎች ላይ በጋራ ለመስራት ያላቸውን ዝግጁነትንም ተናግረዋል። የኤርትራው የትምህርት ሚኒስትር ሰመረ ርዕሶም በቅርቡ በኢትዮጵያ የኤርትራ አምባሳደር ሆነው መሾማቸው የሚታወስ ነው።