ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ነገ ይጀምራል

አዲስ አበባ ጥቅምት 16/2011 የ2011ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ነገ በክልል በሚደረጉ ጨዋታዎች ይጀምራል። በሃዋሳ አርቴፊሻል ስታዲየም ሲዳማ ቡና ከፋሲል ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት የሚያደርጉት ጨዋታ የፕሪሚየር ሊጉ የመክፈቻ ጨዋታ ነው። ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባ ስታዲዮም ከቀኑ 10 ሰዓት የ13ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ አሸናፊው ኢትዮጵያ ቡና ድሬዳዋ ከተማን ያስተናግዳል። በክልል ከተሞች በሚደረግ ጨዋታ ቀጥሎ የአምናው የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ጅማ አባ ጅፋር ወደ አዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም በማምራት ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ከአዳማ ከተማ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ የሊጉን መርሃ ግብር ይጀምራል። በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲዮም በክለቡ ላይ የስያሜ ለውጥ ያደረገው መቐለ ሰብዓ እንደርታ (በቀድሞው መጠሪያ መቐለ ከተማ) ከደደቢትና በሀዋሳ ስታዲዮም ሀዋሳ ከተማ ከወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲ በተመሳሳይ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ። ፕሪሚየር ሊጉን አዲስ የተቀላቀሉት ባህርዳር ከተማ፣ ሽሬ እንደስላሴና ደቡብ ፖሊስ በመጀመሪያው ሳምንት መርሃ ግብር ጨዋታቸውን ማድረግ የነበረባቸው ቢሆንም ያለፈው የከፍተኛ ሊግ ውድድሩ ወደ 2011 ዓ.ም በመራዘሙ ምክንያት "በቂ ዝግጅት ባለማድረጋችን ጨዋታው ይራዘምልን" የሚል ጥያቄ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አቅርበው ነበር። ክለቦቹ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ ጨዋታቸውን በሚቀጥለው ሳምንት እንዲጀምሩ ፌዴሬሽኑ መወሰኑ የሚታወስ ነው። በዚሁ መሰረት ደቡብ ፖሊስ ከመከላከያ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከባህርዳር ከተማና ሽሬ እንዳስላሴ ከወላይታ ድቻ የሚያደርጉት ጨዋታ በዚህ ሳምንት አይካሄድም። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዛሬ በ2011ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መጀመርን አስመልክቶ መግለጫ ይሰጣል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን መግለጫው በስፖርታዊ ጨዋነት ላይ ያተኩራል ተብሎ ይጠበቃል። በሌላ በኩል እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ የወንዶች ፕሪሚየር ሊግ ጥሎ ማለፍ ውድድር በታህሳስ ወር 2011 ዓ.ም እንደሚጀመር አስታውቋል። ታህሳስ 30 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲዮም የአምናው የጥሎ ማለፍ አሸናፊ መከላከያ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ከቀኑ 11 ሰዓት ከ30 ደቂቃ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ሁለቱ ክለቦች በ2010 ዓ.ም የጥሎ ማለፍ ውድደር በፍጻሜው ጨዋታ ተገናኝተው መከላከያ ቅዱስ ጊዮርጊስን በመለያ ምት አሸንፎ ዋንጫውን ማንሳቱ ይታወሳል። የጥሎ ማለፍ ውድድሩ ከፕሪሚየር ሊጉ ጎን ለጎን እንደሚካሄድና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በጨዋታዎቹ ላይ የቀን፣ የቦታና የሰዓት ለውጥ ሊያደርግ እንደሚችልም ኮሚቴው ገልጿል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም