ቀጥታ፡

አዲሷ ፕሬዝዳንት በአገሪቱ ምጣኔ ኃብታዊ፣ ማህበራዊና የፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ለውጥ እንደሚያመጡ ይጠበቃል - አስተያየት ሰጪዎች

አዲስ አበባ ጥቅምት 15/2011 አዲሷ የኢፌድሪ ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በአገሪቱ ምጣኔ ኃብታዊ፣ ማህበራዊ እና የፖለቲካ ሁኔታ ላይ ለውጥ እንደሚያመጡ እምነት እንዳላቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች  ገለጹ። የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ዛሬ ባካሄዱት አስቸኳይ የጋራ ስብሰባ  ሳህለወርቅ ዘውዴን የመጀመሪያዋ የኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ መርጠዋቸዋል። በዚህም ባለፉት አምስት ዓመታት አገሪቱን በፕሬዝዳንትነት ያገለገሉት ዶክተር ሙላቱ ተሾመን በመተካት ለመጪዎቹ ስድስት ዓመታት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሆነው ያገለግላሉ። አዲሷ ፕሬዚዳንት ላለፉት 30 ዓመታት በዓለም አቀፍ፣ በአህጉርና በብሔራዊ ደረጃ በውጭ ግንኙነት ሥራ የካበተ ልምድ አላቸው። በመሆኑም የበኩላቸውን ሚና በመጫወት የአገሪቱን ምጣኔ ኃብታዊ፣ ማህበራዊ እና የፖለቲካ ሁኔታዎች ላይ ለውጥ እንደሚያመጡ እምነት እንዳላቸው አስተያየታቸውን ለኢዜአአ የሰጡ የከተማው ነዋሪዎች ገልፀዋል። አስተያየታቸውን ከሰጡ አቶ አክሊሉ አጥላው    ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሴቶች በፖለቲካውም በማህበራዊውም በመሳተፍ ንቁ ተሳትፎ እዲያደርጉ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩ ለሀገር እድገት ትልቅ  ፋይዳ እንደለው ተናግረዋል፡፡ "በጣም ለአገራችን ጠቃሚ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ እንስት ናቸው እና ወደ ስልጣን መምጣታቸው በእጅጉ ሊበረታታና ሊደገፍ የሚገባው ነው ወደፊትም ለአገራችን ዲፕሎማቲክ ስራ በመስራት ከፍተኛ ለውጥ ያመጣሉ የሚል ሃሳብ አለኝ” ያሉት ደግሞ አቶ መስፍን ከበደ ናቸው፡፡ አቶ ዘላለም ምህረቴ  በበኩላቸው አዲሱ ሹመት  "ሌሎች ሴቶች በተለይ ወጣቶች እንዲበረታቱና ነገ አገራቸው ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ወጣቶች እንዲማሩም ተስፋ የሚጥል ነው ብሩህ ተስፋ የሚያጭር በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ገጽታ የሚቀይር የቀደመ ታሪኳን የሚያመጣ ሁለንተናዊ ገጽታ የሚለውጥ ስለሆነ ውጤታማ መሆን መቻል አለበት።" ከደርግ ሥርዓተ-መንግሥት ውድቀት በኋላ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የሽግግር መንግሥቱ ፕሬዝዳንት እንዲሁም ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ፣ አቶ ግርማ ወልደ-ጊዮርጊስ እና ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ደግሞ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ሆነው አገልግለዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም