ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ሴት ፕሬዚዳንት መመረጡ አገሪቱ ለአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ተምሳሌት መሆኗን ያሳያል - የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች

አዲስ አበባ ጥቅምት 15/2011 አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ የመጀመሪያዋ ሴት የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ሆነው መሾማቸው አገሪቱ ለአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ተምሳሌት መሆኗን ያሳያል ሲሉ የተፎካካሪ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ተናገሩ። የህዝብ ተወካዮችና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች ዛሬ ባካሄዱት ልዩ የጋራ ስብሰባ አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴን የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት አድርጎ ሾሟል። ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች፤ አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ የመጀመሪያዋ ሴት የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ሆነው መሾማቸው አገሪቱ ለአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ለዓለምም ተምሳሌት መሆኗን ያሳየችበት ነው ብለዋል። የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በገዛ ፍቃድ ስልጣን መልቀቅም በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት እየጎለበተ መምጣቱን ያሳያል ብለዋል። ፓርቲዎቹ በመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የተጀመረው መተካካት በታችኛው እርከን ባሉ የሥራ ኃላፊዎችም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።  የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፕሬዚዳንት አቶ አየለ ጫሚሶ በአስቴየታቸው እንዳሉት "ዶክተር ሙላቱ በገዛ ፍቃዳቸው መተካካትን ሲፈጥሩ ዴሞክራሲን በአገራችን ምን ያህል እየሰረፀ እየሄደ እንዳለ ሁለተኛው በአፍሪካ ስልጣን እንደ እርስት ተይዞ የነበረውን ሁኔታ በአፍሪካ ይሄንን ትልቅ የዴሞክራሲ ሜዳ በመፍጠር ኢትዮጵያ የምትጠራበት ሁኔታ ተፈጥሯል"ብለዋል፡፡  "ዛሬ የተደረገው የስልጣን ሽግግር አስተማሪ ነው፤ አንደኛ ፕሬዚዳንቱ ሰላማዊ በሆነ መንገደ ስልጣናቸውን ለማስረከብ ያደረጉት ጥረት በእጅጉ እናደንቃለን። ሁለተኛው ተተኪው ፕሬዚዳንት በሙያ የበለፀጉ ብዙ ጊዜ ኢትዮጵያን በመወከል በተለያዩ ቦታዎች ያገለገሉ እንስት ሲሆኑ በሴትነታቸው ትልቅ አክብሮት አለን ያሉት ደሞየኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ህብረት ምክትል ሊቀመንበር አቶ ገብሩ በርሄ ናቸው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎቹ በፕሬዚዳንቷ በበዓለ ሲመታቸው ያስተላለፉትን መልዕክት በመቀበል ከመንግስት ጋር አንድ የጋራ ቤት እንደሚገነቡ በማሰብ እርስ በእርስ በመደማመጥ፣ በመፈቃቀርና በመተሳሰብ ለአገር ግንባታ እንደሚሰሩም ጭምር ነው ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም