ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ስልጣንን በሰላማዊ መንገድ በማሸጋገር ረገድ በአፍሪካ ትክክለኛ ምሳሌ መሆን ችላለች- አምባሳደሮች

 አዲስ አበባ ጥቅምት 15/2011 በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ ያለው ስልጣንን በሰላማዊ መንገድ የማሸጋገሩ  ሂደት ለአፍሪካ አገራት ትክክለኛ ምሳሌ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው አምባሳደሮች ገለጹ። ሂደቱም የኢትዮጵያን የፖለቲካ እድገት እንደሚያሳይም ዲፕሎማቶቹ አክለዋል። የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ስልጣን በፈቃደኝነት መልቀቅን ተከትሎ ከስድስት ወራት በፊት ዶክተር አብይ አህመድ ሰላማዊ በሆነ ሂደት የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ መያዛቸው ይታወሳል። የህዝብ ተወካዮችና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች ዛሬ ባካሄዱት ልዩ የጋራ ስብሰባ  ደግሞ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመን የስልጣን መልቀቂያ ጥያቄ ተቀብለው በምትካቸው አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴን ሹመዋል። በተቃራኒው በስልጣን ላይ ለመቆየት ሲሉ ህገ-መንግስት እስከ ማሻሻል የደረሱ የአፍሪካ መሪዎች መኖራቸው እሙን ነው። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጉዳዩን አስመልክቶ በኢትዮጵያ የማላዊና ኩባ አምባሳደሮችን አነጋግሯል። አምባሳደሮቹ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በስድስት ወራት ውስጥ ብቻ ሁለት የአገሪቱ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች በምሳሌነት ሊጠቀስ በሚችል  መልኩ ስልጣናቸውን  ለተተኪያቸው አስረክበዋል። በኢትዮጵያ የማላዊ አምባሳደር ችማንጎ ኤድዋርድ ችርዋ ኢትዮጵያ እያደረገችው ያለው የስልጣን ሽግግር ለአፍሪካ ትክክለኛ ምሳሌ መሆኑን ገልጸው፤ አፍሪካውያን በዚህ ሊኮሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።        "ዴሞክራሲ በማውራትና በወረቀት ብቻ አይመጣም" ያሉት አምባሳደሩ፤ ኢትዮጵያ ከዚህ አንጻር ስልጣንን በፈቃድ ከመልቀቅ ባሻገር ሰላማዊ በሆነ ሂደት ለተተኪዎች በማስረከብ የሚበረታታ ጉዞ እያደረገች መሆኑን አውስተዋል። ይህም የአገሪቱን የፖለቲካ እድገት ያሳያል ነው ያሉት። በኢትዮጵያ የኩባ አምባሳደር ቪልማ ቶማስ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እንደመሆኗ በበርካታ ነገሮች ለአፍሪካ ምሳሌ የመሆን ኃላፊነት እንዳለባት ገልጸዋል። በአገሪቱ እየተመለከቱት ያለው ሰላማዊ የሰልጣን ሽግግርም ኢትዮጵያ ይህን ኃላፊነት እየተወጣች መሆኑን እንደሚያሳይ አክለዋል። ኢትዮጵያ ከሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በተጨማሪ ሴቶችን ወደከፍተኛ የመንግስት ሃላፊነት በማምጣትም ከአፍሪካ ባለፈ ለመላው ዓለም ምሳሌ መሆን መቻሏንም አምባሰደር ቪልማ አውስተዋል። የህዝብ ተወካዮችና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች ዛሬ ባካሄዱት ልዩ የጋራ ስብሰባ አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴን የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት አድርገው ሲሾሙ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የበርካታ አገራት ዲፕሎማቶች ሂደቱን በአካል በመገኘት ታዝበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም