ቀጥታ፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከጣልያኑ አቻቸው ጋር በጋራ ጉዳዮች ላይ መከሩ

አዲስ አበባ ጥቅምት 15/2011 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከጣልያኑ አቻቸው ኢንዞ ማውሮ ሚላኔሲ ጋር ትናንት በሮም ተገናኝተው የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት መንገድ ላይ መክረዋል። ዶክተር ወርቅነህ የኢትዮጵያ መንግስትን ከፍተኛ የልኡካን ቡድን በመምራት በጣሊያን እየተካሄደ ባለው ሁለተኛው የጣልያን-አፍሪካ ትብብር የሚኒስትሮች ምክክር መድረክ ላይ በመሳተፍ ላይ ናቸው። ከመድረኩ ጎን ለጎን ከጣሊያኑ አቻቸው ኢንዞ ማውሮ ሚላኔሲ ጋር ባካሄዱት ውይይት በኢንቨስትመንት፣ መሰረተ-ልማት ግንባታ፣ በትምህርትና ባህል ልውውጥ እንዲሁም በንግድ መስኮች በአገራቱ መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር ተስማምተዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳለው ሚኒስትሮች በአፍሪካ ቀንድ የሰላምና ፀጥታ ሁኔታም ላይ መክረዋል። ኢትዮጵጵያና ጣሊያን በቀጠናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም ዓቀፋዊ የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ በመካከላቸው ያለውን ትብብር አጠናክረው ለማስቀጠል የጋራ መግባባት ላይ መድረሳቸውንም ፅህፈት ቤቱ አመልክቷል። ኢትዮጵያ ከጣልያን ጋር ያላትን ጠንካራ የሁለትዮሽ ትብብር ከማሳደግ ጎን ለጎን በጣልያን-አፍሪካ የትብብር መድረክ  ላይ ያላትን ተጠቃሚነት ለማስፋት ትሰራለች ተብሏል። ዶክተር ወርቅነህ በሁለተኛው የጣልያን-አፍሪካ ትብብር የሚኒስትሮች ምክክር መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር "በአፍሪካ ከቀድሞው የተሻለ አበረታች ማህበራዊና ምጣኔ ኃብታዊ እመርታ እየታየ ነው፤ የተሻለ የሰላምና ጸጥታ ሁኔታም እየሰፈነ ነው" ብለዋል። የአፍሪካ አገሮች የልማት ውጥኖቻቸውን ከአፍሪካ ህብረት የ2063 የልማት አጀንዳዎች እና ከተባበሩት መንግስታተ ድርጅት ዘላቂ የልማት ግቦች ጋር በማጣጣም እየሰሩ መሆናቸውን ዶክተር ወርቅነህ ጠቅሰዋል። ይህም የአፍሪካ አገራት መፃኢ ጊዜ ይበልጥ ስኬታማ እንዲሆን እንደሚያስችል ገልፀዋል። በአውሮፓዊያኑ የዘመን አቆጣጠር በ2020 አፍሪካን ከጥይት ድምፅ ነጻ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ የተጀመረው የኢትዮ-ኤርትራ የሰላም ሂደት ገና ከጅምሩ ለቀጠናው ሰላምና ጸጥታ ከፍተኛ መሻሻል ምክንያት መሆን መጀመሩንም አውስተዋል። በሶማሊያና ደቡብ ሱዳን ያለው የሰላም ሁኔታም እየተሻሻለ የሚገኝ መሆኑን የጠቆሙት ሚንስትሩ ኢትዮጵያ ለቀጠናው ሰላምና ጸጥታ መስፈን ጉልህ አስተዋጽኦ እያደረገች መሆኑን አመልክተዋል። በተተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ሆነ በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ ስር ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰላም አስከባሪ ሃይል ካሰማሩ ቀዳሚ የአለም አገራት መካከል ኢትዮጵያ እንደምትጠቀስ አስረድተዋል። ኢትዮጵያ ለቀጠናው ሰላም፣ ጸጥታና ልማት የድርሻዋን ገንቢ አስተዋጽኦ እያደረገች ከመሆኑ በተጨማሪ አስፈላጊ የፖለቲካና የምጣኔ ኃብት  ማሻሻያዎችን በማድረግ ውስጣዊ ሁኔታውን በማጠናከር ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ እየሰራች መሆኑንም ገልፀዋል። ኢትዮጵያና ጣልያን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1889 ነው። የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት በተለያዩ ጊዜያት በሚደረጉ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ የትብብር ስምምነቶች እያደገና እየጎለበተ መጥቷል። የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ ከሁለት ሳምንት በፊት በኢትዮጵያ ባደረጉት የሁለት ቀን ይፋዊ የስራ ጉብኝት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር በኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካና ማህበራዊ ጉዳዮች እንዲሁም በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ መምከራቸው የሚታወስ ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም