ቀጥታ፡

የፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ሹመት በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን እይታ

አዲስ አበባ ጥቅምት 15/2011 የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ስለ አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ሆነው ከተሾሙ በኋላ ስለ ሹመታቸው የተለያዩ ዘገባዎችን በማውጣት ላይ ናቸው። አምባሳደሯ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ዛሬ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 5ኛ ዘመን 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 2ኛ ልዩ የጋራ ስብሰባ ዛሬ ሲካሄድ ባገኙት የሙሉ ድምጽ ድጋፍ ነው። ይህንንም ተከትሎ የዓለም መገናኛ ብዙሃን በፊት ገጻቸው ላይ ስለ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ሹመት በመዘገብ ላይ ይገኛሉ። የአሜሪካው ታዋቂ ዕለታዊ ጋዜጣ ዋሺንግተን ፖስት ባወጣው ዘገባ ''ምክር ቤቶቹ አንጋፋዋን ዲፕሎማት የምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያ ሴት ፕሬዚዳንት አድርጎ መረጠ'' ብሏል። መቀመጫውን በኢትዮጵያ ያደረገው የጋዜጣው የውጭ ጉዳዮች አርታኢ ፖል ሺም አምባሳደር ሳህለወርቅ በተባበሩት መንግስታድ ድርጅት (ተመድ) በተለያዩ የስራ ሃላፊነቶች የሰሩ ዲፕሎማት መሆናቸውን ገልጿል። አምባሳደሯ ፕሬዚዳንት ሆነው መመረጣቸው ባለፈው ሳምንት ከካቢኔ አባላቶቹ 50 በመቶ ሴት እንዲሆኑ መደረጉን ተከትሎ የመጣ ምርጫ በመሆኑ ትልቅ ትርጉም ያለው እንደሆነ በጽሁፉ ላይ አስፍሯል። አምባሳደር ሳህለወርቅ ፕሬዚዳንት ሆነው ከተመረጡ በኋላ ባደረጉት ንግግር ሴቶችን ማክበር ላይ አጽንኦት እንደሰጡና "የሴቶችን ጭቆና የሚያወግዝ ማህበረሰብ መገንባት አለበት" በሚል የተናገሩትን ንግግር ፖል በማሳያነት ጠቅሷል። ለሰላምና አንድነት በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ መግለጻቸውንም አውስቷል። የፕሬዚዳንቷ ሹመት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከ6 ወራት በፊት ወደ ስልጣን ከመጡ ጀምሮ እያከናወኗቸው ያሉ የለውጥ ስራዎች አካል እንደሆነም ገልጿል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሴቶች በፖለቲካው መስክ ያላቸው ተሳትፎ ማደግ እንዳለበት የካቢኔ አባላቱን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበትና በሌሎች አጋጣሚዎች አጽንኦት ሰጥተው እየተናገሩ እንደሆነም ፖል አስረድቷል። ፖል ሺም በጽሁፉ ላይ ፕሬዚዳንቷ ከዚህ በፊት ዲፕሎማት ሆነው ያገለገሉባቸውን ተቋማትና ያከናወኗቸውን ተግባራት በዳራ መልክ አስቀምጧል። የፈረንሳዩ የዜና ወኪል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ''አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ ፕሬዚዳንት ሆነው መሾማቸው ሴቶች በመንግስት ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ ይበልጥ ያሳደገ'' ብሎታል። ባለፈው ሳምንት በነበረው የካቢኔ ሹመት ሴት ሚኒስትሮች በኢትዮጵያ ቁልፍ የሚባሉ ሚኒስትር መስሪያ ቤቶችን መምራት መጀመራቸውንና የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ አህመድ ሆነው መሾማቸው በማሳያነት ተጠቅሷል። የፕሬዚዳንቷ ሹመት በኢትዮጵያ ማህበራዊ ሁኔታዎች ላይ ተጽእኖ የሚያሳድርና ትልቅ ምሳሌ እንደሚሆን መገናኛ ብዙሃኑ በዘገባቸው አስፍረዋል። በአፍሪካ የፖለቲካ ታሪክ ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍና ጆይስ ባንዳ በቅደም ተከተል ላይቤሪያንና ማላዊን በፕሬዚዳንትነት ማገልገላቸውን የዜና ወኪሉ አውስቷል። የታላቋ ብሪታኒያ የብሮድካስት ጣቢያ ቢቢሲ ኢትዮጵያ በታሪኳ የመጀመሪያ ሴት ፕሬዚዳንት አገኘች በሚል የፕሬዚዳንቷን መሾም ገልጾታል። አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ በአፍሪካ በአሁኑ ሰአት ብቸኛዋ ሴት ፕሬዚዳንት እንደሆኑና አንጋፋ ዲፕሎማት እንደሆኑ ጠቅሷል። ከአምባሳደሯ በፊት በአፍሪካ ብቸኛ ሴት ፕሬዚዳንት የሞሪሺየሷ አሜናህ ጉሪብ-ፋኪም እንደነበሩም ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል። የአሜሪካው የብሮድካስት ሚዲያ ሲኤንኤን የአምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ ፕሬዚዳንት ሆነው መሾም በምስራቅ አፍሪካዋ አገር ለሴቶች አዲስ ደረጃ የሰጠና በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አድናቆት የተቸረው ውሳኔ እንደሆነ ገልጿል። ሲኤንኤን የአምባሳደሯን የረጅም ዓመት የዲፕሎማሲ ልምድ አድናቆት የቸረ ሲሆን "ወጣቱ የለውጥ መሪ"  ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተለያዩ መስኮች እያከናወኗቸው ያሉ ስራዎችንም አድንቋል። ዓለም አቀፉ የዜና ወኪል ሮይተርስ የአምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ አምባሳደር ሆኖ መሾም በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ስርአት እየተለወጠ መምጣቱን የሚያሳይ እንደሆነ ገልጿል። የእንግሊዙ ዕለታዊ ጋዜጣ ዴይሊ ሜይል የፕሬዚዳንቷ መሾም በአፍሪካ በህዝብ ብዛት ሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ ሴቶች በፖለቲካው ከፍተኛ የአመራር ደረጃ ያላቸውን ተሳትፎ የሚያጠናክር እንደሆነ አብራርቷል። የደቡብ አፍሪካው ኒውስ 24 በድረ ገጹ እንዳሰፈረው "ኢትዮጵያ የካቢኔ አባላቶቿን ግማሹን ሴት በማድረግ እንዲሆን በመወሰን በዓለም ፍትሐዊ የጾታ ተዋጽኦ ካላቸው ጥቂት አገሮች አንዷ ከሆነች በኋላ በታሪኳ የመጀመሪያ የሴት ፕሬዚዳንት ዛሬ መረጠች" ብሏል። የካናዳው ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ የዚምባቡዌው ዕለታዊ ጋዜጣ ዘ ሄራልድ የናይጄሪያው ዕለታዊ ጋዜጣ ዘ ኔሽን እንዲሁም ሌሎችም ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ የመገናኛ ብዙሃንም አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ሆነው መሾማቸውን በተመለከተ ሰፊ ዘገባ ይዘው ወጥተዋል። አምባሳደር ሳህለወርቅ ባለፉት አምስት ዓመታት አገሪቱን በፕሬዚዳንትነት ያገለገሉትን ዶክተር ሙላቱ ተሾመን በመተካት ለቀጣይ ስድስት ዓመታት ያገለግላሉ።                
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም