ቀጥታ፡

ኮንፌደሬሽኑ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የተጀመረው የሰላም ጥረት ስኬታማ እንዲሆን የበኩሌን እየተወጣሁ ነው አለ

አዲስ አበባ ጥቅምት 15/2011 በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የተጀመረው የሰላም ጥረት ስኬታማ እንዲሆን የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌደሬሽን ገለፀ።    በአገራቱ መካከል ለሁለት አስርት ዓመታት የቆየው አለምግባባት በሰላማዊ መንገድ ማብቃቱ ይፋ መደረጉን ተከትሎ የአገራቱን ግንኙነት የሚያጠናክሩ የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው። ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌደሬሽን በኤርትራ ጉብኝት ያደረገ ሲሆን የኤርትራው አቻውም በቀረበለት ጥሪ መሰረት በዋና ፀሀፊው አቶ ተከስተ ባይረ የተመራ ቡድን ዛሬ አዲስ አበባ ገብቷል። የኮንፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ በአቀባበል ስነ-ስርዓቱ ላይ እንዳሉት፤በሁለቱ አገራት መካከል የተጀመረው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲጠናከርና የበለጠ መቀራረብ እንዲፈጠር ኮንፌደሬሽኑ ሚናውን እየተወጣ ነው። ግንኙነቱ በመንግሥት አደረጃጀት ብቻ ሳይወሰን አስከ ታች ያለው ማህበረሰብ ድረስ ዘልቆ ጥሩ መሰረት ይዞ እንዲጠናከርና በአገራቱ ህዝቦች መካከል የተሻለ አንድነት እንዲመጣ የበኩሉን ተግባር እያከናወነ መሆኑንም ገልፀዋል። በዚህ ረገድ ኮንፌዴሬሽኑ እያከናወነው ያለው ተግባር ለሌሎች መሰል የሲቪክ ማህበራትና አደረጃጀቶች ምሳሌ የሚሆን ነው ሲሉም ተናግረዋል። የሁለቱ አገራት ኮንፌደሬሽኖች ተመሳሳይ ዓላማ ያላቸው በመሆኑ በቀጣይ በአቅም ግንባታና ሌሎች መስኮች ላይ ተደጋግፈው በጋራ መንቀሳቀስ በሚችሉበት መንገድ ላይም በትኩረት እንደሚሰሩ አብራርተዋል። የኤርትራ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌደሬሽን ዋና ፀሃፊ አቶ ተከስተ ባይረ በበኩላቸው በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል "ሰላምም ጦርነትም"  የማይባለው ሁኔታ ባበቃ ማግሥት ወደአዲስ አበባ በመምጣታቸው መደሰታቸውን ገልፀዋል። "በኢትዮጵያ የምናደርገው ጉብኝት የሁለቱን አገራት ትስስር ከማጠናከሩም በላይ በኮንፌደሬሽኖቹ መካከል የልምድ ልውውጥ እንድናደርግ ምቹ ሁኔታ የሚፈጠር ነው" ብለዋል። የኤርትራ ልኡካን ቡድን ከነገ ጀምሮ ለሁለት ቀናት በሚካሄደው የአፍሪካ ቀንድ አገራት የሰራተኞች ማህበራት ኮንፌደሬሽን ምስረታ ጉባኤ ላይ ይሳተፋል። በምስረታ ጉባኤው ላይ የልዑካን ቡድኑን ጨምሮ የስምንት አገራት የሰራተኞች ማህበራት ኮንፌደሬሽኖች ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሏል። የኤርትራ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌደሬሽን ልዑካን ቡድኑ ከመጭው እሁድ ጀምሮ ለአምስት ቀናት በኢትዮጵያ የሚካሄዱ የተለያዩ የልማት እንቅስቃሴዎችን ይጎበኛል።                        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም