ቀጥታ፡

አበረታች ቅመሞችን በመጠቀም የህግ ጥሰት የፈጸሙ አትሌቶች ከአራት እስከ ስምንት ዓመት የሚደርስ ቅጣት ተላለፈ

አዲስ አበባ ጥቅምት 15/2011 የተከለከሉ የስፖርት አበረታች ቅመሞችን በመጠቀም የህግ ጥሰት በፈጸሙ አትሌቶች ላይ ከአራት እስከ ስምንት ዓመት የሚደርስ ቅጣት መጣሉን ብሔራዊ የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ጽህፈት ቤት አስታወቀ። አትሌት ጫልቱ ሹምየና አትሌት ብርቱካን አደባ ቅጣቱ የተላለፈባቸው አትሌቶች ናቸው። አትሌት ጫልቱ ከሚያዚያ 9  እስከ 14 ቀን 2010 ዓ.ም በተካሄደው 47ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ800 ሜትር ውድድር ተሳትፋ በ1 ደቂቃ ከ59 ሴኮንድ ከ99 ማይክሮ ሴኮንድ የሻምፒዮናውን ሪከርድ ጭምር በማሻሻል አሸናፊ መሆኗ ይታወሳል። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ጽህፈት ቤት በዚህ ውድድር ላይ ባደረገው ምርመራ አትሌቷ "ቴስቴስትሮን" የተባለውን የተከለከለ መድሃኒት መጠቀሟን አረጋግጧል። ጽህፈት ቤቱ ጉዳዩን በማጣራት አትሌት ጫልቱ እ.አ.አ ከመስከረም 6 ቀን 2018 እስከ መስከረም 6 ቀን 2022 ድረስ ለተከታታይ አራት ዓመታት በማንኛውም አገር አቀፍም ሆነ ዓለም አቀፍ ውድድር ላይ እንዳትሳተፍ ውሳኔ ማሳለፉን ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። በተጨማሪም በውድድሩ ላይ ላይ ያስመዘገበችው ውጤት እንዲሰረዝና የተሰጣትን የገንዘብና የሜዳሊያ ሽልማት ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እንድትመልስ ቅጣት ተላልፏል። በተያያዘ አትሌት ብርቱካን አደባ ህዳር 7 ቀን 2008 ዓ.ም በቻይና የሻንጋይ ዓለም አቀፍ የማራቶን ውድድር በአበረታች ቅመሞች ምርመራ የተከለከለ መድሃኒት በመጠቀም የህግ ጥሰት መጸፈሟ ተረጋግጦ ለአራት ዓመት እገዳ የተጣለበት መሆኑ ይታወቃል። ይሁን እንጂ አትሌቷ ጉዳዩን ለማጣራት የተሰጣትን ጊዜያዊ እገዳ በመጣስ ጥር ወር 2010 ዓ.ም በባህሬን የሙስካት ማራቶን ላይ ተሳትፋለች። በዚህም ውድድር ላይ በተደረገለት ምርመራ "ፕሬድኒሶሎን" የተባለ የተከለከለ መድሃኒት በድጋሚ መጠቀሟን ለማወቅ ተችሏል። በመሆኑም አትሌት ብርቱካን ቀደም ሲል በፈጸመችው የህግ ጥሰት የተጣለባትን ጊዜያዊ እገዳ በመተላለፍ በሙስካት ማራቶን ላይ መሳተፍ ብቻ ሳይሆን በድጋሚ የተከለከለ መድሃኒት ተጠቅማ ተገኝታለች። በዚሁ መሰረት አትሌቷ ከአሁን በፊት ከተጣለባት ቅጣት በተጨማሪ እ.አ.አ እስከ ሰኔ 22 ቀን 2029 ድረስ ለተከታታይ ስምንት ዓመታት በምንም አይነት ስፖርታዊ ውድድር ላይ እንዳትሳተፍና ያስመዘገበችው ውጤት እንዲሰረዝ ቅጣት ተላልፏል። አገር አቀፍ የስፖርት ማህበራትንና ሌሎችንም ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው የፀረ-አብረታች መድሃኒት እንቅስቃሴ በተለይም የህግ ጥሰት በሚፈጽሙ አካላት ላይ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁሟል። በተለይም በተለያዩ ዓለም አቀፍ የማራቶን ውድድሮች ላይ በግላቸው በማናጀርም ይሁን በሌላ መንገድ ተመዝግበው የሚሳተፉ አትሌቶች በየጊዜው ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚደረግ በመገንዘብ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጽህፈት ቤቱ ጥሪውን አቅርቧል። ሁሉም ባለድርሻ አካላት የፀረ-አበረታች መድሃኒት እንቅስቃሴ ላይ የበኩላቸውን ገንቢ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ተጠይቋል። የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ጽህፈት ቤት በኢትዮጵያ ንጹህ ስፖርት እንዲስፋፋ በማድረግ በትክክለኛው መንገድ ተወዳድረው የሚያሸንፉ ንጹሃን ስፖርተኞች እንዲፈጠሩ ዓላማ ይዞ የሚሰራ ተቋም ነው።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም