የኤርትራ ሰራተኞች ማህበር ኮንፌደሬሽን የልኡካን ቡድን አዲስ አበባ ገባ - ኢዜአ አማርኛ
የኤርትራ ሰራተኞች ማህበር ኮንፌደሬሽን የልኡካን ቡድን አዲስ አበባ ገባ
አዲስ አበባ ጥቅምት 15/2011 በኤርትራ ሰራተኞች ማህበር ኮንፌዴሬሽን ዋና ጸሃፊ አቶ ተከስተ ባይረ የሚመራ የልኡካን ቡድን በኢትዮጵያ የአንድ ሳምንት የሥራ ጉብኝት ለማድረግ ዛሬ አዲስ አበባ ገባ። ይኸው 14 አባላት ያሉት የልኡካን ቡድን አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ሲደርስ የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ተቀብለውታል። ኢትዮጵያና ኤርትራ በቅርቡ በደረሱት የሰላም ስምምነት መሰረት በአገራቱ ህዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ ናቸው። የኤርትራ ሰራተኞች ማህበር ኮንፌዴሬሽን ልኡካን ቡድን የኢትዮጵያ ጉብኝትም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ለማጠናከር የተጀመረው እንቅስቃሴ አንዱ አካል ነው ተብሏል። የልኡካን ቡድን አባላቱ በኢትዮጵያ ቆይታቸው የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽንን ጨምሮ ከተለያዩ አካላት ጋር በመገናኘት በጋራ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ፤ በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያሉ የተለያዩ የልማት ስራዎችንም ይጎበኛል ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህም ሌላ የሁለቱ አገራት ሰራተኞች ማህበር ኮንፌዴሬሽኖች በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነትም ይፈርማሉ። የልኡካን ቡድኑ በኢትዮጵያ ከነገ ጀምሮ ለሁለት ቀናት በሚካሄደው የአፍሪካ ቀንድ የሰራተኞች ማህበር ምስረታ ጉባዔ ላይም ይሳተፋል ተብሏል።