ኢትዮጵያ በፊፋ የአገራት የእግር ኳስ ደረጃ አንድ ደረጃ ዝቅ አለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በፊፋ የአገራት የእግር ኳስ ደረጃ አንድ ደረጃ ዝቅ አለች
አዲስ አበባ ጥቅምት 15/2011 ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማህበር (ፊፋ) ዛሬ ይፋ ባደረገው የጥቅምት ወር የአገሮች ወርሃዊ የእግር ኳስ ደረጃ ኢትዮጵያ በአንድ ደረጃ ዝቅ ብላለች። በዚሁ መሰረት ኢትዮጵያ በመስከረም ወር ከነበረችበት 149ኛ ደረጃ ወደ 150ኛ ወርዳለች። በኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ የሚሰለጥነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሁለት ሳምንት በፊት በ2019 የአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ ከኬንያ ጋር ባደረገው የማጣሪያ ግጥሚያ በሁለቱም ጨዋታዎች ተሸንፏል። በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች ያለ ምንም ግብ ያጠናቀቁ ሲሆን በናይሮቢ ካሳራኒ ስታድየም ላይ በተደረገው ጨዋታ ዋሊያዎቹ 3 ለ 0 በሆነ ውጤት መሸነፋቸው ይታወሳል። በዚሁ ምክንያት ብሔራዊ ቡድኑ በአፍሪካ ዋንጫ የመሳተፍ ዕድሉ ተሟጥጧል። በጥቅምት ወር የአገሮች ወርሃዊ የእግር ኳስ ደረጃ መሰረት ቤልጂየም፣ ፈረንሳይ፣ ብራዚል፣ ክሮሺያና እንግሊዝ ከአንድ እስከ አምስት ያለውን ደረጃ ሲይዙ ኡሯጓይ፣ ፖርቹጋል፣ ስዊዘርላንድ፣ ስፔንና ዴንማርክ ከስድስት እስከ 10 ያለው ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ከአፍሪካ ሴኔጋል 25ኛ በመሆን የቀዳሚነቱን ደረጃ ስትይዝ፣ ናይጄሪያ 44ኛ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ 46ኛ፣ ሞሮኮ 47ኛ፣ ካሜሮን 51ኛ እና ጋና 52ኛ ደረጃን በመያዝ ይከተላሉ። አውሮፓዊቷ ጂብራልታር ስምንት ደረጃዎችን አሻሽላ 190ኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ በወርሃዊው ደረጃ ከፍተኛ መሻሻል ያሳየች ሲሆን በአንጻሩ ሞዛምቢክ ዘጠኝ ደረጃዎችን በማሽቆልቆል 122ኛ ደረጃን በመያዝ በወሩ ከፍተኛ ደረጃ የቀነሰች አገር ሆናለች። የተርክስና ካይኮስ ደሴቶች 211ኛ በመሆን የመጨረሻውን ደረጃ ይዘዋል። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ፊፋ በመስከረም ወር ባወጣው ወርሃዊ የአገራት የእግር ኳስ ደረጃ ስምንት ደረጃዎች በመቀነስ 111ኛ ደረጃ ላይ መቀመጣቸው ይታወሳል። ፊፋ ከሐምሌ ወር 2010 ዓ.ም በዘረጋው አዲስ አሰራር መሰረት የአገሮች ወርሐዊ የእግር ኳስ ደረጃ የሚወሰነው እርስ በርስ የሚጫወቱት የብሔራዊ ቡድኖች ጥንካሬና አገሮቹ የሚያደርጉት የእያንዳንዱ ጨዋታ ክብደት ላይ ነው። ይህም ከዚህ በፊት ፊፋ እውቅና በሰጣቸው ውድድሮች ላይ ብሔራዊ ቡድኖች በየጨዋታው ባስመዘገቡት ውጤት መሰረት የሚሰጠውን የነጥብ አሳጣጥ ያስቀረ ነው። አንድ ብሔራዊ ቡድን በማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ በሚያስመዘግበው ውጤት ለፊፋ የእግር ኳስ ደረጃ የሚያገኘው ነጥብ ከወዳጅነት ጨዋታዎች ውጤት ከሚያገኘው ነጥብ የተሻለ ይሆናል ማለት ነው። የምድብ ጨዋታዎች፣ የማጣሪያ ጨዋታዎች፣ የእያንዳንዱ አገር የሊግና የጥሎ ማለፍ ውድድርና የወዳጅነት ጨዋታዎች የፊፋ የአገሮችን ወርሃዊ የእግር ኳስ ደረጃ ለማስላት ከግምት ውስጥ ያስገባል።