"ማንኛውንም አገራዊ ጉዳይ በብሄር መነጽር ብቻ መመልከት መቆም አለበት" ዶክተር ሙላቱ ተሾመ - ኢዜአ አማርኛ
"ማንኛውንም አገራዊ ጉዳይ በብሄር መነጽር ብቻ መመልከት መቆም አለበት" ዶክተር ሙላቱ ተሾመ
አዲስ አበባ ጥቅምት 15/2011 "ኢትዮጵያውያን በአገሪቱ የሚከሰቱ ምጣኔ ኃብታዊም ሆኑ ፖለቲካ ክስተቶች በብሄር መነጽር ብቻ መመልከት ማቆም አለባቸው" ሲሉ ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ተናገሩ። የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ይህንን ያሉት ለሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ዛሬ የስራ መልቀቂያ ባቀረቡበት ወቅት ባደረጉት የስንብት ንግግር ነው። ዶክተር ሙላቱ በዚሁ ወቅት "በአሁኑ ወቅት ቀላል የሚባለው የመንግስት ውሳኔ ሳይቀር የሚታየው ልዩነትን ማዕከል ባደረገ የብሄር፣ የቋንቋና ሀይማኖት መነጽር እየሆነ መጥቷል" ብለዋል። ለኢትዮጵያ አንድነትና ብሄራዊ እድገት ቀጣይነት የሚበጀው መላው ዜጋ ከዚህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ራሱን ማራቅ ሲችል እንደሆነም ተናግረዋል። አሁን ያለው አስተሳሰብ በዚሁ ከቀጠለ ግን ሁሉም ወደፊት ለማየት የሚሻት ኢትዮጵያ ምኞት ብቻ ሆና ትቀራለች ሲሉም አንስተዋል። "ልዩነታችንና ሕብረ ቀለሞቻችን እንዳሉ ሆነው ስለ ኢትዮጵያዊ ሕብረታችን የምንዘምርበት ዋና ምክንያት አገራዊ አንድነታችን ለሁለንተናዊ ብልጽግናችንና ለህዳሴያችን ዋስትና መሆኑን ልንረሳው አይገባም" ብለዋል። ዶክተር ሙላቱ እንደገለጹት በጥርጣሬ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ልዩነትን ብቻ ማእከል ያደረገ ትርክት በአሸናፊነት ወይም በተሸናፊነት መንፈስ የተቃኘ የፖለቲካ አውድ አገሪቱን ወደ አልተፈለገ አደጋ እንደሚወስዳት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊገነዘበው ይገባል። በአገሪቱ የተጀመረውን ዲሞክራሲያዊ ግንባታ ዘላቂነት ለማረገጋገጥ የዲሞከራሲ ተቋማትን በማይናወጥ መሰረት ላይ ማቆም እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። "የተቋማቱ ኃላፊዎች በገለልተኝነት፣ በነጻነትና በአገልጋይነት መንፈስ መስራት ሲችሉ ሀይማኖት፣ ብሄር ወይም ጾታ የትኩረት ማዕከል መሆኑ ይቀራል ብዬ አምናለሁ" ብለዋል። የሁለቱ ምክር ቤቶች አባላት በዶክተር ሙላቱ ምትክ አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴን የመጀመሪያዋ የኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝዳንት አደርጎ ሾሟል።