ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ስፖርት በዘርፉ ዕውቀትና ግንዛቤ ባላቸው ሰዎች ሊመራ ይገባለ ተባለ

አዲስ አበባ ጥቅምት 15/2011 የኢትዮጵያ ስፖርት ዘርፍ ዕውቀት፣ ግንዛቤና ቁርጠኝነት ባላቸው ሰዎች መመራት እንዳለበት የስፖርት ቤተሰቦች አመለከቱ። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የህዝቡን የእግር ኳስ ጥማት ለማርካት ችግሮችን በጥናት በመለየት እግር ኳሱን ለማሳደግ ያስችላል ያለውን ጥናት አስጠንቶ ውይይት እንዲካሄድበት አድርጓል። በጥናቱ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ የክለብ አመራርና የስፖርት ጋዜጠኞች ተወካዮች ተካተውበታል። በጥናቱ ውጤት ላይ ትናንት በተደረገው ውይይት ላይ የተገኙት የቀድሞ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ተካ አስፋው ሁሉንም ስፖርት በበላይነት የሚመራው አካል ክፍተት እንዳለበት ጠቁመዋል። ስፖርቱ ፍላጎቱና ቁርጠኝነት ባላቸው ሰዎች እየተመራ እንዳልሆነና በዚህ ምክንያት እግር ኳሱም ሆነ ሌሎች የስፖርት ዓይነቶች ችግር ውስጥ መውደቃቸውን ተናግረዋል። መንግስት የስፖርት ዘርፍ ችግርን ለመፍታት ለስፖርቱ ተቆርቋሪና ቁርጠኛ የሆኑ አመራሮችን መመደብ እንዳለበት አመላክተዋል። በቀድሞ አጠራሩ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ማህበራት እውቅናና ድጋፍ  ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ሀዱሽ ገብረስላሴ በስፖርት አመራርነት የሚመጡ ብዙዎቹ ሀላፊዎች የማስፈጸም አቅማቸው ደካማ የሆነና በተቆርቋሪነት የሚሰሩ እንዳልሆኑ ገልጸዋል። በመሆኑም እግር ኳሱም ሆነ ሌሎች ስፖርቶች በዘርፉ ዝንባሌና እውቀቱ ባላቸው ባለሙያዎች ሊመራ እንደሚገባ ጠቁመዋል። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የባህል፣ የቱሪዝና የመገናኛ ኢንፎርሜሽን ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር መስፈን ቸርነት በበኩላቸው በስፖርቱ የሚታዩ ክፍተቶችን ለማረም በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ገለጸዋል። በርካታ የአገሪቱ ህዝብ ተወዳጅነት ያለው እግር ኳስም ሆነ ሌሎች የስፖርት ዓይነቶችን ለማሳደግ በየጊዜው ችግሩን መፈተሽ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም