ቀጥታ፡

በዞኑ በደለል ወርቅ ፍለጋ የተሰማሩ ወጣቶች ከ77 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ አገኙ

ሽሬ እንዳስላሴ ጥቅምት 15/2011 በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ተደራጅተው በባህላዊ መንገድ በደለል ወርቅ ፍለጋ የተሰማሩ ወጣቶች ለብሄራዊ ባንክ ካቀረቡት ወርቅ ከ77ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ገለጹ። ወጣቶቹ በገቢው ኑሮአቸውን እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል። የዞኑ ማዕድንና ኢነርጂ ጽህፈት ቤት አስተባባሪ አቶ ካልአዩ ብርሃነ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ገቢው የተገኘው በዞኑ የደለል ወርቅ ክምችት ባሉባቸው ወረዳዎች በ18 ማህበራት የተደራጁ  ወጣቶች 88 ነጥብ 957 ኪሎ ግራም የወርቅ ደለል ለባንኩ በማቅረባቸው ነው። ገቢው ባለፉት ሦስት ወራት በማህበር የተደራጁት 727 ወጣቶች ባከናወኑት ሥራ መገኘቱን አስረድተዋል፡፡ በዞኑ በሚገኙት ስድስት ወረዳዎች የደለል ወርቅ ክምችት ቢኖርም፤ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ለባንኩ መቅረብ የሚገባው ምርት እንዲቀንስ ማድረጋቸውን አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡ ይህንን ህገ ወጥ ድርጊት ለመከላከልና የተመረተው የደለል ወርቅ ወደ ባንክ ለማቅረብ ለባህላዊ የደለል ወርቅ አምራቾችና ለሚመለከታቸው  አካላት ሥልጠና  እየተሰጠ ነው ብለዋል። “ፍረ ብቃልሲ” በሚል ስያሜ በሚጠራው ማህበር ስር በደለል ወርቅ ፍለጋ የተደራጀው ወጣት በላይ ተክሉ በአስገደ ፅምብላ ወረዳ ከሁለት ዓመታት በፊት በባህላዊ መንገድ በደለል ወርቅ ፍለጋ በመሰማራት እስካሁን ከ80 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን አስረድቶ በገቢው ራሱንና ቤተሰቡን እያስተዳደረ መሆኑንም ተናግሯል፡፡ “ከገቢው የተወሰነውን በመቀነስ የሸቀጣ ሸቀጥ መደብር በመክፈት ታናሽ እህቴ ራሷን እንድትችል አድርጌያለሁ'' ብሏል፡፡ ሌላዋ የማህበሩ አባል ወጣት ስምረት ለገሰ በበኩሏ በገቢው ከእጅ ወደ አፍ የነበረው ኑሮዋን ተሻሽሎ አሁን 40 ሺህ ብር መቆጠቧን ገልጻለች። በዞኑ በየዓመቱ በክረምት ወቅት ከ30 ሺህ በላይ ሰዎች በደለል ወርቅ ፍለጋ ስራ በመሰማራት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ከጽህፈት ቤቱ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም