ቀጥታ፡

ለሴቶች የንግድ ሥራ ፈጠራ ፕሮጀክት ስኬታማነት አመራሩ ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ዲላ ጥቅምት 15/2011 በዲላ ከተማ ለተጀመረው የሴቶች የንግድ ሥራ ፈጠራ ፕሮጀክት ስኬታማነት አመራሩ ተገቢውን ድጋፍና ክትትል እንዲደርግ ተጠየቀ ። የፕሮጀክቱን መጀመር ይፋ ያደረገ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ በዲላ ከተማ ተካሂዷል። የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘነበ ኩሞ በእዚህ ወቅት እንደገለጹት የሴቶች የንግድ ሥራ ፈጠራ ፕሮጀክት ባለፉት አምስት ዓመታት በአዲስ አበባ፣ በአዳማ፣ በሃዋሳ፣ በድሬዳዋ፣ በባህር ዳርና በመቀሌ ከተሞች ተግባራዊ ሲሆን ቆይቷል። በተያዘው በጀት ዓመትም በዲላ፣ አክሱም፣ ጎንደርና አሰላ ከተሞች በፕሮጀክቱ በማካተት የትግበራ ጊዜው ለሁለት ዓመት እንዲራዘም መደረጉን ተናግረዋል። " የፕሮጀክቱ አላማ የነጋዴ ሴቶችን የገቢ አቅም ማሳደግና የስራ ፈጠራ ክህሎታቸውን ማዳበር ነው” ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ፕሮጀክቱ ባለፉት አምስት ዓመታት ተግባራዊ እየሆነ ያለው ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ መሆኑን ገልፀዋል። የፕሮጀክቱ አፈጻጸም ውጤታማ በመሆኑ ከጣሊያንና ጃፓን መንግስታት ተጨማሪ የብድር ገንዘብ በመገኘቱ ፕሮጀክቱ የሚካሄድባቸውን ከተሞች ቁጥር ወደ አስር ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል። በፕሮጀክቱ አዲስ በተካተቱ አራት ከተሞች እስከ ጥር 2012 ዓ.ም ተጨማሪ 2 ሺህ 600 ዴት ነጋዴዎች ተጠቃሚ ለማድረግ ምዝገባ መካሄዱን የገለጹት አቶ ዘነበ፣ በዲላ ከተማ ለተጀመረው ፕሮጀክት ስኬታማነት አመራሩ ተገቢውን ድጋፍና ክትትል እንዲያደርግ ጠይቀዋል። በተለይ በንግድ ሥራ የተሰማሩ ሴት ነጋዴዎች በሥራቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ከክህሎት ስልጠና በተጨማሪ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ አመልክተዋል። በአገር አቀፍ ደረጃ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ዮሐንስ ሰለሞን በበኩላቸው ባለፉት አምስት ዓመታት ፕሮጀክቱ ተግባራዊ በሆነባቸው ስድስት ከተሞች ከተመዘገቡ ከ25 ሺህ በላይ ሴቶች ውስጥ ለ15 ሺህ ዎቹ በሥራ እድል ፈጠራ ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል። ለዘጠኝ ሺህ 500 ሴቶች 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ብድር መሰጠቱንና በብድር ከተሰራጨው ገንዘብ ውስጥም ከ98 በመቶ በላይ ተመላሽ መደረጉን አስተባባሪው ተናግረዋል። አቶ ዮሐንስ እንዳሉት የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ሴቶች በጨርቃጨርቅና ልብስ ስፌት፣ በምግብ ዝግጅት፣ በባልትና ውጤቶች፣ በሸቀጣ ሸቀጥና ሌሎች የንግድ ሥራዎች የተሰማሩ ናቸው። ፕሮጀክቱ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው ዓለም ባንክን ጨምሮ ከተለያዩ አካላት በብድርና በድጋፍ በተገኘ 126 ሚሊዮን ዶላር መሆኑንም ገልጸዋል። የጌዴኦ ዞን ሴቶችና ሕጻናት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ሰናይት ጂግሶ በበኩላቸው በዲላ ከተማ ተግባራዊ መሆን በጀመረው ፕሮጀክት ተጠቃሚ ለመሆን ከተመዘገቡ 425 ሴት ነጋዴዎች ውስጥ 350 ዎቹ የስራ እድል ፈጠራ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል። ስልጠናው በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሴቶች የንግድ ስራ ክህሎታቸውን በማሳደግ የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ በኩል ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል። በመምሪያው በኩል ነጋዴ ሴቶች የወሰዱትን ብድር በአግባቡ ሥራ ላይ አውለው ብድራቸውን መመለስ እንዲችሉ በባለሙያ የታገዘ የማማከር ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አመልክተዋል። ስልጠናውን ከወሰዱ የዲላ ከተማ ሴት ነጋዴዎች መካከል በባህል ምግብ ንግድ ሥራ የተሰማሩት ወይዘሮ ደገፈች መርቲ በስልጠናው የንገድ ሥራቸውነ እንዴት ማሳደግ እንደሚችሉ ተጨማሪ ግንዛቤ መያዛቸውን ገልጸዋል። በጌዴኦ ዞን ሦስት የኢንዱስትሪ መንደሮች በግንባታ ላይ መሆናቸውን የገለጹት ወይዘሮ ደገፈች፣ ስልጠናውና የፕሮጀክት ድጋፉ በቀጣይ በኢንዱስትሪዎቹ ውስጥ ገብተው ለመስራት አቅመ እንደሚፈጥርላቸው ተናግረዋል። በፕሮጀክቱ የሚደረግላቸውን የስልጠናና የገንዘብ ድጋፍ በመጠቀም ቆጮን እሴት ጨምረው በማምረት ለውጭ ገበያ ለመላክ ዕቅድ እንዳላቸውም ተናግረዋል። ወይዘሮ አባይነሽ ገብሬ የተባሉ ነጋዴ በበኩላቸው በስልጠናው በደንበኛ አያያዝ፣ የንግድ ሥራን እንዴት ከትንሽ ወደትልቅ ማሳደግ እንደሚቻልና በዘመናዊ የገንዘብ አያያዝና አጠቃቀም ላይ በቂ ክህሎት መያዛቸውን ገልጸዋል። በቀጣይ በፕሮጀክቱ ሴት ነጋዴዎች በተሰማሩበት ውጤታማ እንዲሆኑ አመራሩ ከእዚህ በፊት ለኢንተርፕራይዞች ከሚያደርገው ድጋፍ ተለየ ትኩረት ሰጥቶ እንዲያግዛቸውም ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም