አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው የሹመት ደብዳቤያቸውን ለሞዛምቢክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቀረቡ - ኢዜአ አማርኛ
አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው የሹመት ደብዳቤያቸውን ለሞዛምቢክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቀረቡ

አዲስ አበባ ጥቅምት 15/2011 በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም የሹመት ደብዳቤ ቅጂያቸውን ለሞዛምቢክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቀረቡ። መቀመጫቸውን በደቡብ አፍሪካ ያደረጉት አምባሳደር ሽፈራው የሹመት ደብዳቤ ቅጂያቸውን ለሞዛምቢክ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሪያ ማኑኤላ ዶ ሳንቶስ ሉካስ ነው ያቀረቡት። አምባሳደሩ በዚሁ ወቅት በኢትዮጵያና በሞዛምቢክ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መወያየታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ አስታውቋል። በውይይቱም ከዚህ ቀደም በሁለቱ አገሮች መካከል በተለያዩ ጉዳዮች በትብብር ለመሥራት እንዲሁም በከፍተኛ ባለሙያዎችና በሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ደረጃ ግንኙነቶችን ለማድረግ የተደረሰውን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ ከወዲሁ ዝግጅት መጀመር እንደሚያስፈልግ ተስማምተዋል። ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን መከላከል፣ በዝውውሩ የተጎጂዎች አያያዝና በአዘዋዋሪዎች ቁጥጥር ዙሪያ እንዲሁም የዝውውሩ መተላለፊያ አገሮች ተቀራርቦ መሥራት እንደሚያስፈልግም ከመግባባት ደርሰዋል። ኢትዮጵያና ሞዛምቢክ ይፋዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የጀመሩት እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ1977 መሆኑ ይታወቃል። በተያያዘ ዜና በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ችግር ለመፍታት እየሰራ ይገኛል፤ የተፈናቀሉ ኢትዮጵያንን ለመርዳት ጥረት እያደረገ ነው ተብሏል። በደቡብ አፍሪካ ፊሪ እስቴት ፕሮቭንስ ሄልብሮን ከተማ የሚኖሩ ባለፉት 10 እና ከዚያ በላይ ዓመታት የቆዩ ኢትዮጵያዊያን ሐምሌ 19 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በአካባቢው በተፈጠረው ሁከት ከሥራ ቦታቸው የተፈናቀሉ ኢትዮጵያዊያን ችግር ለመፍታት ኤምባሲው ጥረት እያደረገ ይገኛል። በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ባለ-ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም እንደገለጹት ኢትዮጵያውያኑ ወደ ሥራ ቦታቸው መመለስ በሚችሉበት ሁኔታ ዙሪያ ከአካባቢው ባለሥልጣናት ጋር ተደጋጋሚ ውይይት እየተደረገ ይገኛል። ጥቅምት 9 ቀን 2011 ዓ.ም አምባሳደር ሽፈራው ወደ ሄልብሮን ከተማ በመጓዝ ከአካባቢው ባለስልጣናት ጋር ውይይት አድርገዋል። ኤምባሲው ወገኖች ወደ ሥራ ቦታቸው እንዲመለሱ የሚችለውን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ እና በቀጣይም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በችግሩ ዙሪያ ተጨማሪ ጥረት ያደርጋል ብለዋል። ኢትዮጵያዊያኑ በበኩላቸው አሁን ያሉበት ችግር ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ ኤምባሲው ሰብዓዊ እርዳታ በሚያገኙበት ሁኔታ በትኩረት እንዲሰራ ጠይቀዋል። በችግሩ ዙሪያ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር አብሮ መስራት አስፈላጊ በመሆኑ በቀጣይ በአካባቢው ከሚገኙ የኢትዮጵያዊ ማህበረሰብ አመራሮች ጋር ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት እንደሚደረግም ተገልጿል።