ቀጥታ፡

የንብ ማነብ ምርታማነትን በማሳደግ ለውጭ ምንዛሬ ለማዋል ይሰራል --- ሚኒስቴሩ

መቀሌ ግንቦት 14/2010 ኢትዮጵያ ለንብ ማነብ ስራ ያላትን አመቺ  የሆነ የአካባቢ ስነ ምህዳር በመጠቀም ከዘርፉ የሚገኘውን  ምርት ለውጭ ምንዛሬ ገቢ ለማዋል በትኩረት እንደሚሰራ የእርሻና የእንስሳት ሃብት ሚኒስቴር ገለጸ። ዓለም አቀፍ የንብና ማር ሲምፖዚየምና ባዛር በመቀሌ ከተማ ተከፍቷል። በዝግጅቱ መክፈቻ የእርሻና የእንስሳት ሃብት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ እንዳሉት፣ ንብ ማነብ እንደሌሎች የግብርና ልማት ዘርፎች ብዙ ወጪና ድካም ሳይጠይቅ በቀላሉ ማልማት የሚያስችል ዘርፍ ነው። " ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የታደለቻቸው የንብ ሃብቶችን በጥንቃቄና እንክብካቤ በመያዝ ጥቅም ላይ በማዋል ከማር ምርት ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል "ብለዋል። ይህም ለሀገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ  ማስገኘት የሚችል ዘርፍ ነው። ዘርፉ በአነስተኛ ካፒታል፣ እውቀትና ቦታ ላይ ከፍተኛ የስራ ዕድል የመፍጠር  ጠቀሜታ ቢኖረውም  እስካሁን የተከናወነው ስራ  አነስተኛ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል። ሀገሪቱ ለንብ ማነብ ስራ ያላትን አመቺ  የሆነ የአካባቢ ስነ ምህዳር በመጠቀም የዘርፉን ምርታማነት በማስፋፋት ለውጭ ምንዛሬ ገቢ ለማዋል በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ንብ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ነጋ በቃና በበኩላቸው፣ "በማር ምርት ላይ ለውጥ ለማምጣት ብዙ መስራትና ማስተዋወቅ ያስፈልጋል" ብለዋል። በሀገሪቱ ከ7 ሺህ በላይ ለንብ ቀለብ የሚውሉ የእጽዋት ዝሪያዎችና ከ2 ሚሊዮን  በላይ አናቢዎች ቢኖሩም የዘርፉ  ልማት የሚካሄደው በአብዛኛው በባህላዊ መንገድ በመሆኑ የሚገኘው  ምርትና ገቢ ዝቅተኛ መሆኑን አስረድተዋል። ኢትዮጵያ በንብ ማነብና በማር ምርት ያላትን አመቺነት ተጠቅማ የዘርፉን ልማትና ገቢ ለማሳደግ ባለድርሻ አካላት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስተያየታቸውን የሰጡት የትግራይ ክልል ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አትንኩት መዝገበ ናቸው። ከዘርፉ የሚገኘውን የማር ምርት መጠን ለማሳደግም ክልሉ ከተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ልማት በተጓዳኝ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም አመልክተዋል። "በትግራይ ከ224ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በንብ ማነብ ስራ ተሰማርተው ይገኛሉ"  ያሉት በቢሮው የእንስሳት ሃብት የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ጀማል ግደይ ናቸው፡፡ ከአርሶ አደሮቹ በየዓመቱ ከ25ሺህ በላይ ቶን ለማግኘት የሚያስችል አቅም ቢኖራቸውም እየተገኘ ያለው የማር መጠን ግን 8 ሺህ ቶን ያህል መሆኑን ጠቅሰዋል። " ጥራቱ የጠበቀ ማር በብዛት ለማምረት  በክልል ደረጃ ዘመናዊ ቀፎዎች ለአርሶአደሮች እንዲዳረስ እያደረግን ነው " ብለዋል አስተባባሪው። ትናንት በተከፈተው ሲምፖዚየምና ባዛር  የፌደራልና የክልሉ  መንግስት ስራ ኃላፊዎች፣ የዘርፉ ምሁራን፣ በዘርፉ ልማት የተሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች ፣ ሞዴል ንብ አናቢ አርሶ አደሮችና ማህበራት እየተሳተፉ ነው።                        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም