ቀጥታ፡

የባቡር መስመር ዝርጋታው በቂ መተላላፊያ የለውም፤ ካሳም ሊከፈለን ይገባል....በአፋር የተለያዩ ወረዳ ነዋሪዎች

ሰመራ ጥቅምት 14/2011 ለአዋሽ-ኮምቦልቻ የባቡር መስመር ዝርጋታ ለሰዎችና ለእንስሳት በቂ መተላላፊያ ባለመኖሩና ተገቢ የካሳ ክፍያ ባለመከፈሉ ተቸግረናል ሲሉ በአፋር ክልል የተለያዩ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በበኩሉ በየደረጃው  ከሚገኙ የክልሉ አመራሮችና ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን ችግሩን ለመፍታት እንደሚሰራ አስታውቋል፡፡ በአፋር ክልል የተለያዩ ወረዳዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት የአዋሽ-ኮምቦልቻ የባቡር መስመር ዝርጋታ ለሰዎችና ለእንስሳት  በቂ መተላላፊያ የሌለው በመሆኑና ተገቢው የካሳ ክፍያ በወቅቱ ባለመከፈሉ ተቸግረዋል፡፡ በክልሉ የዱለሳ ወረዳ ነዋሪ ወጣት መሐመድ ሀሰን ከአዋሽ እስከ ኮምቦልቻ የሚሰራው የባቡር መስመር በአካባቢያቸው የተለያዩ መንደሮችን አቋርጦ እንደሚያልፍ ተናግሮ የተዘረጋውን የባቡር ሀዲድ አቋርጦ ለማለፍ ህብረተሰቡ አስከ 1 ኪሎ ሜትር መጓዝ እንደሚጠበቅበት ገልጿል፡፡ ለመሸጋገሪያ የሚሆን በቂ ማቋረጫ ባለመኖሩ ህብረተሰቡ  በተለይም አቅመ-ደካሞች እየተቸገሩ መሆናቸውን የተናገረው ወጣቱ  በሽተኞችና ነፍሰጡር እናቶች በቀላሉ የአምቡላንስ አገልግሎት እንዳያገኙ እንቅፋት መሆኑንም ጠቁሟል፡ የአዋሽ-ፈንታሌ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሀሰን አሊ ወደአዲስ አበባ የሚልፈው የባቡር መስመር በቂ የእግረኛ ማቋረጫ እንዲኖረው ባለመደረጉ በአካባቢያቸው በተደጋጋሚ ጊዜ እንስሳት እየተገጩ ጉዳት መድረሱን አስታውሰዋል፡፡ "ከአዋሽ ወደ ኮምበልቻ የሚሰራው የባባር መሰመርም  በተመሳሳይ  መልኩ በቂ ማቋረጫ ስለሌለው በሰዎችና በእንስሳት ላይ አደጋ እንዳያስከትል ከወዲሁ ተገቢ ማስተካከያ እንዲደረግለት ቢጠየቅም መልሰ ሊሰጥ የሚችል አካል አልተገኘም" ብለዋል፡፡ የእሳቸውን ቤት ጨምሮ የ76 አባውራዎች መኖሪያ ቤት እንደፈረሰ የተናገሩት ነዋሪው አስካሁን ተገቢውን ካሳ እንዳልተከፈላቸው አስታውቀዋል፡፡ ከእዚህ በተጨማሪ 115 ሄክታር የወል መሬት ላይ የነበረ እጽዋትና የእንስሳት መኖ ተመንጥሮ ቦታው ለመንገድ ስራ ቢውልም ክፍያ አንዳልተፈጸመላቸው ተናግረዋል፡፡ የአዋሽ-ፈንታሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አባሃባ ሁሴን በበኩላቸው "የካሳ ክፍያው ያልተከፈለው ህብረተሰቡ የአኗኗር ዘይቤው ከቦታ ወደቦታ ተንቀሳቃሽ መሆኑና በእዚህም ካርታ ሲነሳም ሆነ ጥናቱ ሲካሄድ ሰዎቹ በወቅቱ በቦታው ላይ ስላልነበሩ ነው" ብለዋል፡፡ ይሁንና የባቡር መንገድ ሥራው ሲጀመር አርብቶ አደሮቹ በቦታው ላይ መልሰው ሰፍረው ስለነበረ ቤታቸው እንደፈረሰባቸው አስረድተዋል፡፡ አርብቶ አደሮቹ የአካባቢው ህጋዊ ነዋሪ በመሆናቸውና የአኗኗር ባህላቸው አስገድዷቸው የተፈጠረ ችግር በመሆኑ እንደ ሌሎቹ የአካባቢው ነዋሪዎች ተገቢው ካሳ እንዲከፈላቸው ከምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ጋር በመነጋገር ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ተፈራ በበኩላቸው የፕሮጀክቱ ግንባታ ሲጀመር ባቡር በሚያልፍባቸው አካባቢዎች ከይዞታቸው የሚነሱ ነዋሪዎች ቋሚ ተክሎችና የእርሻ መሬቶች አስፈላጊውን ካሳ ለመክፈል በተደረገው ጥናት መሰረት ለተነሺዎቹ ክፍያ መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡ አሁን በወረዳዎቹ ቅሬታ እያቀረቡ የሚገኙት ግለሰቦች የካሳ ጥናቱ በተካሄደበት ወቅት በአካባቢው ያልነበሩና ከጥናቱ በኋላ መጥተው በቦታው ላይ የሰፈሩ በመሆናቸው የአሰራር ህጉ የማይፈቅድ በመሆኑ ኮርፖሬሽኑ ካሳ ለመክፍል እንደማይችል አስረድተዋል፡፡ የወል መሬትን ካሳ ክፍያን በተመለከተ  ከህብረተሰቡ ለተነሳው ጥያቄ የካሳ ክፍያ የሚፈጸምበት የህግ አግባብ ባለመኖሩ የካሳ ክፍያ የሚፈጸመው የባለቤትነት ካርታ ወይም የይዞታ ማረጋጋጫ ላላቸው ንብረቶች ብቻ መሆኑን የኮምዩኒኬሽኑ ዳይሬክተሩ አክለው ገልጸዋል፡፡ ከማቋረጨ መንገድ ጥያቄ ጋር ተያይዞ ለቀረበው ቅሬታም "የሰዎችና የእንስሳት እንቅስቃሴ ከሚበዛባቸው ቦታዎች በስተቀር ማቋረጫ እንዲኖር አይፈለግም" ያሉት ዳይሬክተሩ፣ የባቡር መንገድ ሥራው ሲጀመር ህብረተሰቡን ባሰተፍ መልኩ የማቋረጫ ቦታዎች መመረጣቸውን አስታውሰዋል፡፡ ህብረተሰቡ አርብቶ አደር እንደ መሆኑ መጠን ከቦታ ቦታ እንደልቡ መንቀሳቀስ እንዲችል መስተካከል ያለባቸው ማቋረጫዎች ካሉ ከወረዳው አመራሮችና  ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን በቀጣዩ ሳምንት ቦታው ድረስ በአካል በመገኘት የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ ጥረት እንደሚደረግ አቶ ደረጀ ተናግረዋል፡፡ የአዋሽ-ኮምቦልቻ 270 ኪሎ ሜትር የባቡር መስመር ግንባታ በ2007 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረ ሲሆን ከሚኖረው ምጣኔ ሀብታዊ  ጠቀሜታ ባለፈ የአፋርና አማራ ክልል ህዝቦችን ሁለንተናዊ ትስስር ለማጎለበት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም