ቀጥታ፡

የሮቤ -ጋሰራ 60 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ስራ በመቋረጡ ተቸግረናል - የጋሰራ ወረዳ ነዋሪዎች

ጎባ ጥቅምት 14/2011 የግንባታ ስራው ከአንድ ዓመት በፊት የተጀመረው የሮቤ -ጋሰራ 60 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ስራ በመቋረጡ መቸገራቸውን አስተያየታቸውን የሰጡ የጋሰራ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ ከነዋሪዎች መካከል አቶ አብዱልጀዋድ ከማል በሰጡት አስተያየት ከአንድ ዓመት በፊት የግንባታ ስራው የተጀመረው የሮቤ - ጋሰራ መንገድ ስራ በመቋረጡ መቸገራቸውን ገልፀዋል፡፡ ''መንግስት ከአንድ ዓመት በፊት መንገዱን ወደ አስፋልት ደረጃ ለማሳደግ ወስኖ ስራ ተጀምሮ ስናይ የዘመናት ጥያቄያችን በመመለሱ በጣም ተደስተን የነበረ ቢሆንም የመንገዱ ግንባታ ተመልሶ በመቋረጡ አዝነናል'' ብለዋል፡፡ ሌላው የወረዳው አርሶ አደር አቶ አሰፋ በቀለ በበኩላቸው ከዚህ በፊት መንግስት ለመንገዱ ያደርግ የነበረው ጥገና መንገዱ ወደ አስፋልት ደረጃ እንዲያድግ ስራ በመጀመሩ ምክንያት በመቆሙ መንገዱ ለከፋ ብልሽት ተዳርጓል፡፡ ''መንገዱ በመበላሸቱ የትራንስፖርት ችግር እየገጠመን በመሆኑ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት መፍትሄ እንዲሰጠን እንጠይቀለን'' ብለዋል፡፡ የመንገድ ስራውን ኮንትራት የወሰደው የአፍሮጽዮን ኮንስትራክሽን ተቋራጭ  ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ምስጋነው በስልክ እንደገለጹት  የመንገዱን ሁኔታ በተፈለገው ሁኔታ ለማከናወን የአርሶ አደሩ ይዞታ የካሳ ክፍያ መዘግየትና በአካባቢው ላይ የነበረው ዝናባማ የአየር ሁኔታ ማነቆ ሆኖባቸዋል፡፡ ''አሁን ያለው የአየር ሁኔታ ለስራው አመቺ በመሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ በትኩረት እንሰራለን'' ብለዋል፡፡ የባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሲራጅ አብዱልጀባር ''ለስራው መዘግየት የዝናብ መብዛት ሳይሆን ድርጅቱ ለስራው የሰጠው ትኩረትና ክትትል አናሳ በመሆኑ ነው'' ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር  ሀብታሙ ተገኝ በበኩላቸው ችግሩን በማስመልከት የአካባቢው ማህበረሰብ ያነሳው ቅሬታና ስጋት አግባብነት እንዳለው ገልፀዋል፡፡ ግንባታውን በተመለከተ በድርጅቱ በኩል መስተካከል ያለባቸው ሁኔታዎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ኢንጂነሩ እንዳሉት ተቋራጩ በዚህ ዓመት በተለየ ሁኔታ ለውጥ በማምጣት በተያዘለት የጊዜ ገደብ ውስጥ ስራውን ሰርቶ እንዲያስረክብ በመንግስት በኩል አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ይደረግለታል፡፡ የዞኑ ህብረተሰብ በተደጋጋሚ ቅሬታ የሚያነሳባቸውን ሌሎች የሮቤ -ደሎ መና -መዳ ወላቡና ሮቤ- ጎሮ -ጊኒር መንገዶችን ችግር ለመቀረፍ ባለስልጣኑ የአጭርና ረዥም ጊዜ እቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በአጭር ጊዜ በተመረጡ ቦታዎች ላይ ደረጃውን የጠበቀ ጥገና በማድረግ ችግሩን ለመፍታት እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡ ባለስልጣኑ የመንገዱን ችግር  በዘላቂነት ለመፍታት ከመንግስት ጋር በመነጋገር ውሳኔ የሚሰጥበት እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡ የሮቤ-ጋሰራ 60 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ባለፈው ዓመት ደረጃውን ወደ አሰፋልት ለማሰደግ በሶስት ዓመት የጊዜ ገደብ በ800 ሚሊዮን ብር ጨረታውን ያሸነፈው የአፍሮጽዮን ኮንስትራክሽን ድርጅት ስራ መጀመሩ ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም