ቀጥታ፡

ባለስልጣኑ 8 የመንገድ ፕሮጀክቶችን በ14 ቢሊዮን ብር ሊያስገነባ ነው

አዲስ አበባ ጥቅምት 14/2011 የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ስምንት የአስፋልት መንገድ ግንባታ ኮንትራት ስምምነት ተፈራረመ። የመንገዶቹ ርዝመት 6 መቶ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን ለግንባታው 14 ቢሊዮን ብር ወጪ ተይዟል። የመንገድ ግንበታው ወጪ በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ሲሆን ስምንቱም ፕሮጀክቶች በሶስት ዓመት ይጠናቀቃሉ ተብሎም ይጠበቃል። የመንገዱን ግንባታ ለማከናወን ከተፈራረሙት ስምንት ተቋራጮች ውስጥ ሶስቱ አገር በቀል ናቸው። ጣርማ በር-መለያ-ሰፊ ሜዳ መለያ- ሞላሌ- ወገሬ፣ ጅማ- አጋሮ-ዴዴሳ ወንዝ፣ መሰል-ኮራ-ቴሩ፣ አርሲ-ሮቤ-አጋርፋ-አሊ-ኮንትራት 1አሊ ከተማ-ዋቤ ድልድይ፣ አዲ አርቃይ-ጠለምት፣እስቴ-ስማዳ እንዲሁም ውቅሮ-አጽቢ የሚገነቡ መንገድ መንገዶች ናቸው። መንገዶቹ ቀደም ሲል በአስፋልትና በጠጠር መንገድ ደረጃ የነበሩ ሲሆን ካላቸው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታ አንጻር በአስፋልት ደረጃ እንደሚገነቡ ተገልጿል። ስምምነቱን የፈረሙት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሰልጣን ዋና ዳሬክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኝ እንዳሉት ፕሮጀክቶቹ ማህበረሰቡ ለረዥም ጊዜ ጥያቄ ሲያቀርብ ከነበሩት ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው። መንገዶቹ የማህበረሰቡን የትራንስፖርት እንቅስቃሴ የሚያሳልጡና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ፋይዳቸው የጎላ መሆኑንም አንስተዋል። ህብረተሰቡ የመንገዶችን መገንባት በጉጉት የሚጠብቅ በመሆኑ ግንባታው ፈጥኖ መጀመር እንዳለበትም አሳስበዋል። እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ በመንገድ ግንባታ በተደጋጋሚ የሚነሱ የጥራት ችግሮች በነዚህ ፕሮጀክቶች ላይም እንዳይኖር ተቋራጮች በሰው ሃይልና በመሳሪያ ራሳቸውን ማዘጋጀት ይኖርባቸዋልም ብለዋል። ተቋራጮቹ በገቡት ስምምነት መሰረት በጥራትና በተያዘለት ጊዜ ሰርተው እንዲያጠናቅቁም አሳስበዋል። ስምምነቱን የፈረሙት የስራ ተቋራጮች በበኩላቸው በፈረሙት ስምምነት መሰረት በተያዘላቸው ጊዜና ጥራት ሰርተው እንደሚያስረክቡ አረጋግጠዋል። ጣርማ በር-መለያ-ሰፊሜዳ መለያ-ሞላሌ-ወገሬ ግንበታ የሚያከናውነው የመከላከያ ኮንስትራክሽን ማኔጅንግ ዳሬክተር ኢንጅነር ወልዳይ በርኽ የዲዛይን መዘግየት ግንባታው በተያዘለት ጊዜ እንዳይጠናቀቅ ሊያደርግ ስለሚችል ዲዛይኑ በፍጥነት እንዲሰራ ጠይቀዋል። መንገዶቹ ግንባታቸው ሲጠናቀቅ በአካባቢው የነበረውን የትራንስፖትር ችግር በመፍታት፣ የግብርና ምርቶችን ወደ ገበያ ለማምጣትና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ተብሏል። በተጨማሪም ለአካባቢው ማህበረሰብ የስራ አድል በመፍጠር፣ ከተማን በማስፋፋት፣ የጤና፣ ትምህርትና ሌሎች አገልግሎቶችን ለማስፋፋት አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሎም ይጠበቃል። በፊርማ ስነስርአቱ ላይ ከባሌ ዞን ጃርሶ ወረዳ የአካባቢው ማህበረሰብን ወክለው የመጡት አቶ አሊ ኢብራሂም፣ አርሲ-ሮቤ-አጋርፋ-አሊ ኮንትራት 1አሊ ከተማ-ዋቤድልድይ መንገድ እንዲሰራላቸው ለአመታት መጠየቃቸውን ይናገራሉ። መንገድ ባለመኖሩ እናቶችን ጤና ተቋም ለማድረስና የግብርና ምርታቸውን ወደ ገበያ ለማድረስ መሰቃየታቸውን በመግለጽ ዛሬ ጥያቄአቸው በመመለሱ ደስታቸውን ገልጸው ግንበታው እስኪጠናቀቅ ድረስ ከተቋራጩ ጋር እንደሚሰሩ ነው የገለጹት። ጣርማበር-መለያ-ሰፊሜዳ መለያ-ሞላሌ-ወገሬ መከላከያ ኮንስትራክሽን፣ አዲ አርቃይ-ጠለምት የንኮማድ ኮንስትራክሽን፣ ውቅሮ-አጽቢ ሱር ኮንስትራክሽን የሚገነቡ ሲሆን ቀሪዎቹ በቻይና የተለያዩ የግንባታ ተቋራጮች ይገነባሉ። የመንገዶቹ ግንባታ በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ የአካባቢው ማህበረሰብ፣ መስተዳድሮችና ሌሎችም ትብብር እንዲያደርጉ ተጠይቋል። ዛሬ የተፈረመው የመንገድ ግንባታ ስምምነት በሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እድቅ ለመገንባት ከተያዘው አካል ነው ተብሏል። በቀጣይ ሳምንት ሌሎች ስድስት የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ስምምነቶች እንደሚደረግም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም